የሰላም ስምምነቱ ዓለም ዐቀፋዊ ድጋፍ እያገኘ መሆኑ ተጠቆመ

ኅዳር 23/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ መንግስት እና በሕወሓት መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት ዓለም ዐቀፋዊ ድጋፍ እያገኘ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ አለም ተናገሩ።

አምባሳደር መለሰ አለም ስምምነቱ ዓለም ዐቀፋዊ ድጋፍ በማግኘቱ ሀብት ማሰባሰብ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በድህረ ጦርነት ወቅት በጦርነቱ የተፈናቀሉት ዜጎችን መልሶ ማቋቋም እና ወደ ቄያቸው የመመለስ ስራ ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተግዳሮት ውስጥ ዲፕሎማሲያዊ ስኬትን ማስመዝገቧን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

ይህንን ስኬት ለማስፋትና ለማጽናት በፈረንጆቹ 2023 በውጭ ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ወደ ሀገር መጥተው ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል ተብሏል።

ለዲፕሎማቶች አቅም በመፍጠር በድህረ ጦርነት ሀብት የማሰባሰብ እና የኢትዮጵያን ገጽታ እንዲገነቡ ማስቻል ያስፈልጋል ብለዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ባለፈው ሳምንት 4ሺሕ 300 ኢትዮጵያዊያን ከዛምቢያ፣ የመንና ከሳውዲ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተነግሯል፡፡

በመስከረም ቸርነት