የፋይናንስ ዘርፍ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ  ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች  በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው  – የብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ

ኅዳር 23/2015 (ዋልታ) በፍትህና በፀጥታ ዘርፍ የኢፌዲሪ የፋይናንስ ዘርፍ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ቴወድሮስ በቀለን ጨምሮ የመረጃና ደህንነት አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ከተቋቋመና ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዝ መጀመሩንና ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ወደ ስራ መግባቱን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እና የፍትህ ሚኒስቴር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚቴው በሦስት ንዑስ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን የህግ፣ የመረጃና የፋይናንስ ኮሚቴ ስለመሆናቸው ተነግሯል።

ብሔራዊ ኮሚቴው እስካሁን በሰራቸው ስራዎችና በኮሚቴው አስፈላጊነት ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የኢፌዲሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና ተገን በማድረግ በሀገር ሀብትና ንብረት ላይ ዘረፋ መፈፀሙንና የሙስና ወንጀል የብሔራዊ ደህንነት ስጋት እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።

የሙስና ወንጀልን ለመከላከል ብሎም በሀገር ላይ የዝርፊያ እና የተለያዩ የሙስና ወንጀሎች የሚፈፅሙትን አካላት ተጠያቂ ለማድረግ ነው ብለዋል።

የመንግስትን ሙሉ አቅም በመጠቀም ከህዝብ ጋር በመሆን ይህን አደጋ ለመቀልበስ እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል።

የኢፌዲሪ የፍትህ ሚኒስትር ጌዴዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ኮሚቴው ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ የተለያዩ ጥናቶች መደረጋቸውንና በተለይ በመሬት አስተዳደር ዘርፍ የተሰሩ የሙስና ወንጀሎች ለመለየት መቻሉ የተነገረ ሲሆን የአርሶ አደር ልጆች በማስመሰል ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት 175 ሺሕ ካሬ መሬትና ኮንዶሚኒየም ቤቶችን በቦሌ፣ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ እና በሌሎች አካባቢዎች የመሬት ዝሪፊያ ያደረጉ አመራሮች ተይዘዋል ምርመራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።

በፍትህና በፀጥታ ዘርፍ የኢፌዲሪ የፋይናንስ ዘርፍ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ የመረጃና ደህንነት አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑም ተነግሯል።

ምርመራው በሌሎች ተቋማት እንደሚቀጥልና በተለይም ሀብት ያላስመዘገቡ አመራሮች ተጠያቂ ለማድረግ ይሰራል ተብሏል።

በሳራ ስዩም