“የሰሞኑ ጭጋጋማ አየር ከትንበያው አንጻር የሚጠበቅ ነው” ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ


ሐምሌ 21/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሰሞኑን እየታየ ያለው ጭጋጋማ አየር ከክረምቱ የአየር ትንበያ አንጻር የሚጠበቅ እንደሆነ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።
በጭጋጋማው አየር የሚከሰተው የእይታ መጋረድ ጉዳት እንዳያስከትል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በክረምት ዝናብ ተጠቃሚዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ሊመዘገብ እንደሚችል ኤጀንሲው በትንበያው ማመላከቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በተለይም የምስራቅ አጋማሽ በሚል የሚጠሩ አካበቢዎች በአብዛኛው መደበኛና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ መተንበዩን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ሰሞኑን የተከሰተው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የክረምት ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች የታየና በክረምቱ ወቅት የሚጠበቅ ክስተት መሆኑ ግንዛቤ መወሰድ አለበት ብለዋል።
ጭጋጋማ አየር በኢትዮጵያ ለአጭር ጊዜ በሐምሌና በነሐሴ ወራት የሚታይ ነው፤ የአየር ሁኔታው “ዘላቂነት ላይኖረው ይችላል” ነው ያሉት አቶ ፈጠነ።
የዚህ አይነት ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ እይታን የሚጋርድ እንዲሁም እይታዎች በአጭር ርቅት የተገደቡ እንዲሆኑ የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል።
የእይታ መጋረድ በአየርና በየብስ ትራንስፖርት ላይ ተጽእኖ የሚያደርስ በመሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕና ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር በቅንጅት በመስራት ጭጋጋማው አየር ከአየር ትራንስፖርት ጋር የሚኖረውን ተጽእኖ አስመልክቶ ዕለታዊ መረጃዎችን ለተቋማቱ እየሰጠ እንደሆነም ነው አቶ ፈጠነ ያስረዱት።
የሚሰጡትን መረጃዎች መሰረት በማድረግ ተቋማቱ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉም ብለዋል።
በየብስ ትራንስፖርትም አሽከርካሪዎችና መንገደኞች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከጭጋጋማው አየር በተጨማሪ ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚጥልባቸው አካባቢዎች የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያሻ ጠቁመዋል።
በተለይም የሚዘንበው ዝናብ በግብርና ምርቶች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በማሳ ላይ የሚንሳፈፈውን ውሃ የማጠንፈፍና የውሃ ቦይ መቅደድ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በከተሞች የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎችን መጥረግና የጎርፍ ማሳለጫ መንገዶች ማበጀት እንደሚገባና ከተማ አስተዳሮች ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
ለጎርፍ ተጋላጭ በሆነ በረባዳማ መሬት ላይ የሚኖሩ ዜጎች በዝናብ ምክንያት አደጋ እንዳይደርስባቸው ድጋፍ ማድረግ፤ ዜጎችም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም መክረዋል።
የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በተለይም በተፋሰሶች የጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራዎች ማከናወን እንደሚገባና፤ በዚህ ረገድም ከሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በክረምቱ እየጣለ ያለው ዝናብ ሊያደርሰው የሚችለውን አሉታዊ ጉዳት በመቀነስ ዝናቡ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች መጠቀም ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።