የውጭ ጣልቃ ገብነትን በሀገራዊ አንድነት መመከት

(በብርሃኑ አበራ)

ሐምሌ 21/2013(ዋልታ) – ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ እና በአሸባሪው የህወሓት ትንኮሳ ምክንያት በሀገሪቱ በሰሜኑ ክፍል የተፈጠረውን ችግር መሰረት በማድረግ ኃያላን ነን የሚሉ ሀገራትና የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጭምር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት በመጣር ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በግልጽ ቋንቋ እኛ ልጆችሽ በህይወት እያለን ማንም ኢትዮጵያን “እኔ አውቅልሻለሁ” ሊል አይችሉም በማለት አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ ከመግለጽ አልፈው የሰራዊቱ አባል ለመሆን ወደ ማሰልጠኛ ተቋማት በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡

አሸባሪው ህወሃት በሀገር መከላከያ ሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት እና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ላይ የጸጥታ ችግር ማጋጠሙን ተከትሎ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትና ፈላጭ ቆራጭ መሆን የሚሹ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እየበረታባ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ የተነሳ በተለያዩ ጊዚያቶች በሀገር ውስጥ እና በሁሉም የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን “ብሔራዊ ክብር በህብረት”፣ “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ”፣ “ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የሚያደርጉት ተጽዕኖ ሉዓላዊነትን የሚጥስ ነው”፣ “ግድቡ የኔ ነው” የሚሉና መሰል መልዕክቶችን በማሰማት የአደባባይ ተቃውሞ ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡

እንዲሁም በዘመኑ በስፋት ጥቅም ላይ በሚውሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ጭምር ህብረ- ብሔራዊነትን በአንድነት አጉልተው የሀሳብ ዘመቻዎችን በማድረግ ተቃውሟቸውን ከጀመሩ ወራትን አስቆጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሀገሪቱ የራሷን የውስጥ ጉዳይ እንዴት መምራት እንዳለባት ሊነገራት እንደማይገባ አስምሮ ቢያስረዳም ጣልቃ ገብነትን የሚቃወሙ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ቢሰጥም ፈላጭ ቆራጭ መሆን የሚያምራቸው ውሳኔ እናሳልፍ መፍትሔ እንጠቁም ባይ ኃያላን ሀገራት ሁሉንም “አውቅላችኋለሁ” ከማለት አለመቆጠብ ግን የሀገራቱን አላማ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ኢስያ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ረዳት ፕሮፌሰር እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቁት ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በነበራቸው ቆይታ ኃያላን ሀገራት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ከሚያደርጉት ጣልቃ ገብነትና ከሚያሳድሩት ጫና በስከጀርባ ያለውን ስውር ዓላማ በዝርዝር አብራርተውታል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ከሌሎች አህጉራት አንጻር ያላት አምራችና ርካሽ የሰው ሀይል፣ የከርሰ ምድርና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች በተጨማሪ የዓለም ሀገራት የሚመላለሱበት እና መርከቦች የሚተላለፉበት በመሆኗ የኃያላን ሀገራት ቀልብ ስባለች ይላሉ ተመራማሪው ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ፡፡ ኃያላኖቹ ቀደም ሲል ሀይልን በመጠቀም የአፍሪካ ሀገራትን በቅኝ ግዛት ተቀራምተው በመዘበሩት ሀብት ህዝባቸውን አስተምረው፣ ኢኮኖሚያቸውን አበልጽገው፣ ሀገር አቅንተው አሁን ላይ በተጨባጭ የሚስተዋለው ልዩነት እንዲመጣ ያደረጉ መሆናቸውንም አያይዘው ይገልጻሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሀገራት የተመኙትን በእጃቸው ለማስገባት ሀይል በማይንጸባረቅበት መልኩ ዕርዳታ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ድጋፍ እና ሌሎች አወንታዊ የሚመስሉ ተጽዕኖዎችን በማድረግ ስልታዊ ቅኝ አገዛዝን እያስፋፉ እንደሆነም የአፍሪካና ኢስያ ጉዳዮች አጥኚ እና ተመራማሪው ይጠቁማሉ፡፡ ኃያላን ሀገራት ቀጣይ ህልውናቸውን ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በታዳጊ ሀገራት ላይ በሚፈጸመው ብዝበዛ ጣልቃ ገብነትን እንደ ሁነኛ ቁልፍ በመጠቀም ከፋፍሎ እርስ በእርስ በማናቆር የጦርነትና የውድቅት መክፈቻ አድርገውታል፡፡

ዶክተር ሳሙኤል እንደሚገልጹት ኃያላኖቹ የተበዝባዥ ሀገራትን ጥንካሬን ስለማይፈልጉ ልክ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን እንደገጠማት እራሳቸውን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ አስመስለው በመከፋፈል፣ በማጋጨት፣ የጦር መሳሪያዎችን በመቸርቸር ሲሻቸውም አላስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ በተለይ ደግሞ ኃያልነታቸውን በመጠቀም በዕርዳታ ድርጅቶችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ተጽዕኖ በማድረግ የማዳከምና የማሽቆልቆል ስራን ይሰራሉ፡፡ የውጭ እርዳታ ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር በሚያቀርቡት ሰብዓዊ ድጋፍ የሰውን ህይወት ማትረፍ እጅግ የሚመሰገን ተግባር ቢሆንም ድርጅቶች የመንግስታቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ በመሆናቸው የሀገርን ሉዓላዊነት ሲሸረሽሩ እንደሚስተዋሉ ነው አጥኚና ተመራማው የሚናገሩት፡፡

በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚፈናቀል ህዝብ ከሌለ፣ የሚከፋፈልና እርስ በእርስ የሚታኮሰ ማህበረሰብ ካልተፈጠረ፣ ያልተረጋጋና ቀውስ ውስጥ የገባ ቀጠና ካልተስተዋለ የኃያላን ሀገራትን ከፍታ ስለሚሸረሽር ድህነትን የሚቀርፍ ስደትን የሚያስቀር እንደ ህዳሴ ግድብ ዓይነት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ከመደገፍ እና ከማበረታታት ይልቅ በሀገር አፍራሽ አሸባሪዎች ተርታ መሰለፍን ጣልቃ ገብ ሀገራት ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ የተለያዩ የጥናት ጽሁፎች ያስረዳሉ፡፡

በዕርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ ከድህነት የወጣ ሀገር በታሪክ እንደሌለ ደግሞ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ እና የዋልታ ሚድያና ኮምኒኬሽን የማህበራዊ ሚድያ ክፍል ዋና አዘጋጅ ጳውሎ በለጠ ይገልጻሉ፡፡

ጳውሎስ እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ እና ጸሀፊ ግራም ሀንኮክ በጉዳዩ ዙሪያ መጽሀፍ መጻፉን ገልጾ፣ ግራም የድህነት ባላባቶች (Lorsds of Poverty) ሲል በሰየመው መጽሀፉ ይህንን ጉዳይ በስፋት አብራርቶታል ሲል ሀሳቡን ያጠናክራል፡፡

ይህንን አሳሪና ስልታዊ የሆነ ዘመናዊ የባርነት ቀምበር አጢኖ በመረዳት በተለይ በአሁኑ ወቅት በስፋት የሚስተዋለውን የኢትዮጵያዊነት የመረዳዳት፣ የመተባበርና ፈጥኖ ደራሽነት ባህል አጠናክሮ በመቀጠል ህብረ-ብሔራዊነት የተረጋገጠባት፣ አንድነት የጸናባት፣ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተጽእኖን የመቋቋም አቅም በውስጣዊ አንድነት መጎልበት እውን ሲሆን የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ ቀጠና እንዲሆን ያስችላል፡፡ ለዚያም ነው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው የበለጸገች ፣ በወታደራዊ አቅሟ የፈረጠመች ስልጡን ሀገር እንድትሆን ዜጎች ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ በሀገር ፍቅር ስሜት በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ጠንክረው ቀን ከሌት መስራት የሚኖርባቸው፡፡

ይህን ማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እየደረሰባት ያለውን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትና ጫናን በቁርጠኝነት መዋጋት እና አሽቀንጥሮ መጣል ያስችላል፡፡ ያኔ ኢትዮጵያውያን በሄዱበት ሁሉ ብሔራዊ ክብራቸው ይጠበቃል፡፡