የሲሚንቶን ምርት ለማሳደግ በትኩረት መሥራት ይገባል ተባለ

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) የሲሚንቶን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በውይይቱ ላይ እንደ ሀገር በአሁኑ ወቅት በሲሚንቶ አቅርቦት ላይ እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

የአምራቾችን፣ የነጋዴዎችን ብሎም የተጠቃሚውን አንጻራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሲሚንቶ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት ተገቢ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ላለው የሲሚንቶ እጥረት መንስኤው የሲሚንቶ ማምረቻ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አለመሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የንግድ ሥርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በልሁ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ለተከሰተው የሲሚንቶ እጥረት ሌላኛው መንስኤ የፍላጎት በእጥፍ መጨመር ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የሲሚንቶ ምርት የኮንትሮባንድ እና የሙስና ምንጭ ሊሆን ስለሚችል ዘርፉ በጥንቃቄ እና በጥሩ ሥነ ምግባር መመራት እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW