በእድሜ ትልቋ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በ99 ዓመታቸው አረፉ

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) በኬኒያ በእድሜ ትልቋ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በ99 ዓመታቸው አረፉ፡፡

በኬኒያ ኤልዶሬት ከተማ ነዋሪ የነበሩት ፕሪሲሊያ ሺሺን በ98 ዓመታቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መጀመራቸው በርካቶችን ያስደነቀ ነበር፡፡

አዛውንቷ ቅድም አያት ከሚሆኗቸው ልጆች ጋር በክፍል ውስጥ ተገኝተው ፊደል ሲቆጥሩ ማየት ለብዙዎች አስደናቂ የነበር ሲሆን ትምህርት እድሜ አይገድበውም የሚለውን በተግባር ያሳዩና ለበርካቶችም ተምሳሌት መሆን የቻሉ ናቸው፡፡

የመንደራቸው የልምድ አዋላጅ የነበሩት እኚህ አዛውንት የልምድ እውቀታቸውን በሳይንስ ለመደገፍ ወደ ትምህርት ቤት ማምራታቸውን ተናግረው እንደነበርም መረጃው አስታውሷል፡፡

አሁን ግን እርጅና ተጫጭኗቸው በ99 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ማለፋቸውን የኬኒያው እስታንዳርድ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ጎጎ ወይም አያቴ በሚል ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት ፕሪሲሊያ ሺሺን በድንገት ታመው መሞታቸውን ነው ቤተሰቦቻቸው ያስታወቁት፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW