የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን እንደተቻለ ተገለጸ

ሰለሞን ሶካ

ሚያዝያ 26/2015 (ዋልታ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በተከናወነ የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል ሥራ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ገለጸ፡፡

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በዋናነት የሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነት፣ የሳይበር ደኅንነት ስጋት፣ የሳይበር ጥቃት ዒላማ የተደረጉ ተቋማት እና የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥርን መሠረት አድርገው ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ በሀገራችን 4 ሺሕ 422 የሳይበር ጥቃቶች እና የጥቃት ሙከራዎች የተፈፀሙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 4 ሺሕ 272 ምላሽ የተሰጠባቸው እና 150 ያህሉ ዒላማቸውን የመቱ እና ጉዳት ያደረሱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም አስተዳደሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሠራቸው ሥራዎች የሳይበር ጥቃት ሙከራን የመመከት አፈፃፀሙን 94.86 ከመቶ ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል።

የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ቢደርሱ ኖሮ የመሠረተ-ልማቶችን ማቋረጥ፤ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ሥራዎች እንዳይሠሩ በማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ገቢ የማስተጓጎል፤ የዳታዎች መሠረቅ እና መጥፋት፤ ዳታዎችን በመመስጠር የቤዛ ክፍያ ገንዘብ መጠየቅ፤ የግንኙነት መንገዶችን በመጥለፍ እና የክፍያን መንገድ በመጠቀም ገንዘብን በማጭበርበር እና በመውሰድ ጉዳት ይደርስ ነበር ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው አብራርተዋል።

የሳይበር ጥቃት ዒላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኛዎቹ ትኩረታቸውን በባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ማድረጋቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት፣ ሚዲያ ተቋማት፣ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት፣ ሚኒስቴሮች፣ የክልል ቢሮዎች፣ የሕክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥቃት ዒላማዎች እንደነበሩም አንስተዋል።

በሀገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ስለተከሰቱ የሳይበር ጥቃት ዓይነቶች እና ኢላማዎች ማብራሪያ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት ዓይነቶች መካከል የድረገጽ ጥቃት፣ ማልዌር፣ የመሠረተ ልማት ቅኝት (Scan)፣ የመሠረተ ልማት ማቋረጥ (DDOS)፣ ሰርጎ የመግባት ሙከራ እንደየቅደም ተከተላቸው ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ የተደረገባቸው እንደነበሩ ገልጸዋል።

በተያያዘም በተለያዩ ዘርፎች በሚገኙ 80 ተቋማት (34 የመንግሥት እና 46 የግል) በተደረገ የተጋላጭነት ዳሰሳ ጥናት የዌብ፣ የኔትዎርክ መሠረተ ልማት፣ የሞባይል መተግበሪያዎችን ጨምሮ በተለያዩ መሠረተ ልማቶች ላይ 486 የሳይበር ደኅንነት የተጋላጭነት የአደጋ ደረጃ (Vulnerability risk level) ክፍተት መገኘቱን እና ከነዚህ ውስጥ 129 የሚሆኑት ከፍተኛ፣ 217 መካከለኛ እና 140 የሚሆኑት ዝቅተኛ የሥጋት ደረጃ ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም አስተዳደሩ የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ወስጥ ለማስገባት ፈቃድ ከተጠየቀባቸው 3123 የተለያዩ ዓይነት የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች መካከል 453 የሚሆኑት የደኅንነት ስጋት የሚያስከትሉ በመሆናቸው አደገኛ ተብለው የተለዩ ቴክኖሎጂዎች በመሆናቸው ወደ ሀገር እንዳይገቡ መደረጋቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት አደጋ ደረጃ ለማመላከት በተመረጡ አራት ዘርፎች (የሚድያ ተቋማት፣ የጤና ተቋማት፣ የፀጥታ እና ደኅንነት እንዲሁም ቁልፍ መሠረት ልማት የሚያስተዳድሩ ተቋማት) ላይ ትኩረት በማድረግ የሳይበር ደኅንነት ስጋትን እና ተጋላጭነትን በማጣመር መሠራታ መቻሉን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

እንደ አጠቃላይ አስተዳደሩ ሊደርሱ የነበሩ ጥቃቶችን በማስቀረት፣ የደረሱ ጥቃቶችን በመመከት፣ እንዲሁም አደገኛ የደኅንነት ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመቆጣጠር ሊደርሱ የሚችሉ ሀገራዊ ጉዳቶች ማዳኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሀገራችንን የዲጂታል ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል ብሔራዊ ጥቅማችንን በሳይበር ምህዳሩ ላይ ያስጠብቃል ሲሉም ገልፀዋል፡፡