ታሪክን በወቅቱና በጊዜው ሰንዶ ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባ ተገለጸ

ሚያዝያ 26/2015 (ዋልታ) ታሪክን በወቅቱና በጊዜው ሰንዶ ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት በመካሄድ ላይ የሚገኘው “ቃል፣ ተግባር፣ ትውልድ” የተሰኘ የመጽሐፍ ዐውደ ርዕይ “ጽናት ያስገኘው ስኬት” በሚል የውይይት ርዕስ ተካሂዷል።

3ኛ ቀኑን በያዘው ውይይቱ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሀገሪቱ የተካሄዱ ዓበይት ታሪካዊና ሀገራዊ ኩነቶችን፣ አዳዲስ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግሮች የያዙት “ከመጋቢት እስከ መጋቢት” እና “ከመስከረም እስከ መስከረም” መጻሕፍት ይዘቶች በፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር አበባው አያሌው ገለፃ ተደርጎባቸዋል።

የታሪክ ምሁር የሆኑት አበባው አያሌው ትውልድ ትምህርት የሚቀስመው ከመልካም ነገርና ከችግር መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ ደግሞ ታሪክን በወቅቱና በጊዜው ሰንዶ ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

“ታሪክ ዛሬ ካልተሰነደ፤ ነገ አይኖርም” ያሉት የታሪክ ምሁሩ “ከመጋቢት እስከ መጋቢት” እና “ከመስከረም እስከ መስከረም” መጻሕፍት ይህንን ግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው ብለዋል፡፡

የመሪዎች ንግግር በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ መጽሐፎቹ ያለፉት አንድ ዓመት ተኩል ዜና መዋዕሎች ናቸው ሊባል ይችላሉ ሲሉም ገልጸዋል።

ታሪክ ሲባል ያለፈን ብቻ ሳይሆን አሁናዊ ሁኔታዎችንና የወደፊቱንም ጉዳይ የሚያመላክት መሆን አለበት፤ የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የተከናወኑት ኩነቶች ትልልቅ ፋይዳ የነበራቸው ናቸው፤ እነርሱን በመጽሐፍ ሰንዶ ማስቀመጥ ደግሞ መጪው ትውልድ ታሪክን በዐውዱ ልክ ለመረዳት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎም ቢሆን እንደ መንግስት በተወሰዱ ትልልቅ የፖሊሲ እርምጃዎች ኢኮኖሚው ከሚጠበቀው በላይ እምርታን አሳይቷል ሲሉ አብራርተዋል።

መንግስት በወቅቱ የወሰዳቸው እርምጃዎች በመጽሐፍ መሰነዳቸው እንደ ሀገር የመጣንባቸውን መንገዶች ለማመላከት ፋይዳቸው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በደረሰ አማረ