የሴቶችን የአመራርነት ተሳትፎ ለማጎልበት ያለመ ውይይት ተካሄደ

የካቲት 26/2013 (ዋልታ) – የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ከ’ዩኤን ውሜን’ ጋራ በመተባበር ላለፉት 30 ዓመታት የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት እና ሴቶች በአመራርነት ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ የመጀመርያ ሴት ሚኒስትር አምባሳደር ታደለች ወልደሚካኤልን ጨምሮ በርከታ የቀድሞ ሴት አመራሮች፣ አሁን ያሉ ሴት አመራሮች እና የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ ያለፈው ትውልድ ሴት አመራሮች የሚደነቅ ስራ መስራታቸውን ገልጸው ይህን ለማስቀጠል በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

ሴቶችን የማብቃት ስራ በሚፈለገው ልክ አለመሰራቱን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ለዚህም ሁሉም በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አክለውም በቀጣይ የሚከበረው ‘ማርች 8’ ከተለያዩ የህግ ተቋማት ጋር ሴቶችን የተመለከተ ምክክር እንደሚደረግ እና ስምምነትም እንደሚፈረም ገልጸዋል፡፡

(በሜሮን መስፍን)