የሶማሊያ መንግሥት አልሸባብ ይዟቸው የነበሩ ሁለት ቁልፍ ከተሞችን አስለቀቀ

የሶማሊያ ወታደሮች

ጥር 9/2015 (ዋልታ) የሶማሊያ ወታደሮች በማዕከላዊ ጉሙዱግ ክፍለ ግዛት አልሸባብ ይዟቸው የነበሩ ሁለት ከተሞች መቆጣጠራቸውን ተናገረ።

የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድር መሐመድ ኑር የመንግሥት ኃይሎች እና የአካባቢዎቹ ተዋጊዎች ሃራርዴሬ እና ጋልካድ ከተሞች መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ቪኦኤ እንደዘገበው ሃራርዴሬ የተባለችው ቁልፍ የባህር ጠረፍ ከተማ የባህር ላይ ዘራፊዎች ዋና መናኻሪያ ስትሆን አልሸባብ ጉልሙዱግ ውስጥ ከተቆጣጠራቸው ስፍራዎች ሁሉ በስትራተጂያዊነቷ ከፍተኛውን ቦታ የያዘች መሆኗ ተመልክቷል።

የሶማሊያ መንግሥት በተጨማሪም የታጣቂውን ቡድን የገቢ ምንጭ ለማድረቅ በሚወስደው ዕርምጃ ከቡድኑ ጋር ንክኪ ያላቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ የባንክ ሂሳቦች እና ተንቀሳቃሽ የገንዘብ ማስተላለፊያዎች መዝጋቱን አስታውቋል።