የቃር መንስኤ እና መፍትሔዎቹ

#ጤና_ደጉ

የቃር መንስኤ እና መፍትሔዎቹ

በቴዎድሮስ ሳህለ

ሚያዝያ 26/2015 (ዋልታ) ቃር በአማርኛ ሥነ ቃል ውስጥ በስፋት ይታወቃል፡፡ ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል፣ ከረሃብ ቃር ይሻላል እና ኧረ እንኳን ህመም ቃርም አያውቀው የሚሉ ቃርን የተመለከቱ አባባሎች ከንግግሮቻችን ውስጥ ጠፍተው አያውቁም፡፡

ቃሉ ከምግብ እና ጤና ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን ቃር የምንለው ወይንም በህክምና አጠራሩ Heartburn በመባል የሚታወቀው የህመም አይነት ሲሆን ብዙ ሰዎችን የሚያጋጥም እጅግ የተለመደ የጤና ችግር ነው።

ቃር የሚከሰተው በጨጓራችን ውስጥ የተመረተ አሲድ ወደ ጉሮሯችን በተደጋጋሚ ሲመለስ ነው፡፡ ይህ በተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ምክንያት የተፈጠረ ከፍ ያለ አሲድ ወደ መዋጫ ጉሮሮ ፍልቅ እያለ ያቃጥላል፤ ምቾትም ይነሳል፡፡

በደረት አካባቢ የማቃጠል ስሜት መሰማት በአብዛኛው ከምግብ በኋላ እና ስንተኛ የሚብስ ችግር ነው። ይህም የሚከሰተው የጨጓራ ውስጥ አሲድ ወደ ላይኛው የምግብ አስተላላፊ ቱቦ (esophagus) ሲመለስ ነው።

የቃር ህመም መንስኤዎች፡-

• ቅመም የበዛባቸው ምግቦችን መመገብ
• ሲትረስ አሲድ ያላቸው እንደ ሎሚ እና ብርቱካን የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን መመገብ
• ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች
• የአልኮል መጠጦችን መውሰድ
• ካፊን ያላቸውን መጠጦች መውሰድ
• ጭንቀት እና ፍርሃት
• የአንዳንድ ሆርሞኖች መጠን መጨመር ለምሳሌ ኢስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን
• ከመጠን በላይ መመገብ
• ከመጠን ያለፈ ውፍረት
• ነፍሰጡርነት ናቸው።

ቃርን ለማስታገስ መደረግ ያለባቸው የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች

• የሰውነት ክብደትዎን ማስተካከል
• ቃርን የሚያስነሱ እና የሚያባብሱ ምግቦችን አለመመገብ
• ከመተኛታችን ከ2 እስከ 3 ሰዓታት ቀደም ብሎ መመገብ
• እያራራቁ በትንሽ በትንሹ መመገብ
• የአልኮል መጠጦችን አለመውሰድ ወይም መቀነስ
• ሲጋራን አለማጤስ
• በመኝታ ጊዜ ጭንቅላትዎን ከፍ ባለ ትራስ ላይ ማሳረፍ ናቸው።

ሃኪምዎን ማማከር የሚገባው መቼ ነው

የቃር ህመም በአብዛኛው በቤት ውስጥ በቀላሉ ሊስተካከል የሚችል የጤና ችግር ነው፡፡ በቀላሉ ልንወስዳቸው ከምንችላቸው እርምጃዎች ውስጥ አመጋገብን በማስተካከል እና ቀስቃሽ የሆኑ ምግቦችን እና ሁኔታዎችን ማስወገድ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ህመሙ ደረጃው ከፍ በሚልበት ወቅት እና የሚከተሉት ምልክቶች ሲከሰቱ የጤና ባለሙያን ማማከር ይገባል፤
• በደረት ላይ ብዙን ጊዜ ምግብ ከተመገቡ በኋላና ማታ ማታ የሚከሰት የማቃጠል ህመም ስሜት ሲከሰት
• ሲተኙ (ጋደም ሲሉ) ወይም ሲያጎነብሱ ማቃጠሉ የሚባባስ ከሆነ
• የአፍ መምረር ወይም አሲድ ጣዕም ያለው ስሜት
• በሳምንት ውስጥ ከሁለት ጊዜ በላይ የሚያቅርዎ ከሆነ
• ለመዋጥ የሚችገሩ ከሆነ
• ማቅለሽለሽና ማስመለስ ስሜት ካለ
• የምግብ ፍላጎት በማጣት ወይንም ለመመገብ በመቸገር ምክንያት የሰውነት ክብደትዎ ከቀነሰ ሃኪም ማማከር ይገባል።