ሰላምን የማፅናትና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው

ሚያዝያ 25/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ሰላምን የማፅናት እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርዶስ በቀለ ጋር ተወያይተዋል።

በኔፓድ የልማት መርኃ ግብሮች አተገባበር እና የሀገራት ሚና ላይ ያተኮረው ውይይት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት የኔፓድ የልማት መርሃግብሮች በአፍሪካ ድህነትን ለመቀነስ እየተደረገ ላለው ጥረት ጉልህ እገዛ አለው።

ለልማት መርኃ ግብሮቹ ተፈፃሚነት ኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶም ደመቀ ለዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ሰላምን የማፅናት እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ኔፓድ በአህጉሪቱ የሚያከናውናቸውን የልማት ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርዶስ በቀለ በበኩላቸው የኔፓድ መርኃ ግብሮች የአፍሪካ የህብረት አጀንዳ 2063 በሚል ለያዛቸው የእድገት እቅዶች መሳካት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ኔፓድ የወጠናቸውን እቅዶች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ያሉ የፋይናንስ ጉድለቶችን ለመሙላት የሃብት ማሰባሰብ ስራ አስፈላጊ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገልፀዋል።

ኔፓድ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የልማት ትብብር በግብርና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርኘራይዞች እንዲሁም መሰል የልማት መስኮች በትብብር እንደሚሰሩ በውይይቱ ተገልጿል።