የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጀመረ

ጥቅምት 12/ 2014 (ዋልታ) በየዓመቱ ጥቅምት በገባ በ12 ቀን የሚካሄደው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጀመረ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ በየዓመቱ ጥቅምት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በተደነገገው መሰረት የሚደረገውን ጉባኤ ክፍተዋል፡፡

‹‹ምእመናን እየበዙ ቃሉን በትክክል እየተገበሩ ከሆነ ሰርተናል ማለት ነው፤ ነገር ግን ምግባርና ግብራቸው ሌላ ከሆነ መስራት ይቀረናል›› ሲሉ በንግግራቸው ገልፀዋል።

በጉቤኤውም ይህንን እንደሚያጤኑ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ገልፀዋል።

እምነትንና አገልግሎትን ለመፈፀም ሰላም መሰረት ነው የተባለ ሲሆን በአሁን ወቅት በአገሪቱ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ቤተክርስትያን እና በምዕመናን ላይ መከራ እና እንግልት መድረሱም ተጠቅሷል።

አገር ሰላም እንድትሆን ምዕመናን በፆም በፀሎት መትጋትና ፈጣሪን መማፀን እንደሚያስፈልጋቸውም አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
በሃኒ አበበ