የበልጉ ዝናብ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቆመ

ሚያዚያ 29/2013 (ዋልታ) – እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል ከውዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።

በብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በሚያዚያ ወር ትንበያ መሰረት በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልሎች እንዲሁም መካከለኛውና ምዕራብ ትግራይ ክልል፣ የደቡብ ክልል መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል።

በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ከዝናቡ መጠን መጨመር ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።

በብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የአየር ትንበያ መሰረት በቀሪው የበልግ ወቅት ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች መለየታቸውን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት በኦሮሚያ ምዕራብ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ አርሲ፣ ቦረና፣ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ የጎርፍ ስጋት መኖሩን ተጠቁሟል።

በሶማሌ ክልል ሸበሌ፣ አፍዴር፣ ሊበን፣ ዶሎ፣ ፋፋን፣ ሲቲ፣ ዳዋ አንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ ሊኖር እንደሚችልም ተገምቷል።

በደቡብ ክልል ሀዲያ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ዳውሮ፣ ሰገን፣ ስልጤ፣ ጉራጌ አንዳንድ አካባቢዎችም የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ተገልጿል።

በሲዳማ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማና የገጠር ቀበሌዎችም የዝናቡን መጠን መጨመር ተከትሎ የጎርፍ ስጋት መኖሩን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

በመሆኑም ለጎርፍ ስጋት ተጋላጭ ለሆነው ማህበረሰብ የቅድመ ጥንቃቄና ወቅታዊ መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።

በብሔራዊ የጎርፍ ግብረኃይልና በክልሎች ግብረኃይል መካከል ተከታታይነት ያለው መረጃ ልውውጥ እንዲኖር የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ኢዜአ ዘግቧል።