የበረዶ የጤና ጥቅሞች

በረዶ በቅርባችን መጠቀም ከምንችላቸውና ብዙ ወጭ ከማይጠይቁ የህክምና ግብዓቶች አንዱ ነው። ብዙ ጊዜ ስፖርተኞች ግጭት ሲያጋጥማቸው በረዶ በላስቲክ አድርገው የተጎዳው አካላቸው ላይ ሲያደርጉ ይስተዋላል። አሁን አሁን በረዶ በሳይንስ የተደገፈ የህክምና አካል እየሆነ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በረዶ ለምን ለምን ህክምና ይውላል ለሚለው ጥያቄ ከዚህ በታች የተወሰኑ ነጥቦችን እንይ፡-

ሀ. ህመም ማስታገሻ፡- ግጭት ወይም አደጋ በደረሰበት ቦታ ላይ በረዶ መያዝ ህመሙ እንዳይሰማን በማድረግ ቁስለት እንዳይፈጠር ያስችለዋል። ይህ ህክምና በተለይ ለወለምታ፣ ለቅጥቅጥና መጋጋጥ ውጤታማ ነው።

ለ. እብጠትን ለመቀነስ፡- ጉዳት በደረሰበት ቦታ ላይ በረዶ መያዝ እብጠት እንዳይፈጠር እና እንዳይጨምር ያስችላል። በረዶ በባህሪው የደም ስሮችና ጡንቻ እንዲኮማተር በማድረግ ደም ወደተጎዳው አካል እንዳይፈስና እብጠት እንዳይፈጠር ያደርጋል፣ ቁስለትም እንዳይፈጠር ይከላከላል።

ሐ. ከህመም  የማገገም ሂደትን ያፋጥናል፡- በረዶ ጉዳት የደረሰበት አካል እንዳያብጥና ቁስለት እንዳይፈጠር ከማድረግ በተጨማሪ ሰውነታችን በፍጥነት እንዲድን የማድረግ አቅም አለው።

መ. ለጡንቻ ጉዳት ማገገም፡- አትሌቶችና የልዩ ልዩ ስፖርት ተወዳዳሪዎች ከከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በኋላ የጡንቻ መጠዝጠዝን ለማስወገድ በበረዶ ውስጥ ይነከራሉ።

ሠ. በረዶ ከባድ የራስ ምታትን ያስታግሳል፡- በረዶን በላስቲክ ጭንቅላት ላይ አድርጎ በማቆየት የከባድ ራስ ምታት (ማይግሪን) ህመምን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ረ. የደም ዝውውርን ያሻሽላል፡- ሙቅ እና ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ መጠመቅ የሰውነታችንን የደም ዝውውር እንዲሻሻል ያደርገዋል። የሙቅና ቀዝቃዛ ሁኔታ መቀያዬር ሰውነታችን እንዲነቃቃ በማድረግ ደም ወደ ሁሉም የሰውነታችን አካል በጥሩ ሁኔታ እንዲደርስ ያደርጋል።

ሰ. ለስሜት መነቃቃት፡– በረዶ ውስጥ ስንነከር ሰውነታችን ኢንዶርፈን የተባለ ሆርሞን ያመነጫል። ሆርሞኑ ስሜትን ከፍ እና ዘና በማድረግ የደስታ ስሜት ይፈጥራል።

በአጠቃላይ በረዶ የጡንቻን የማገገም ጊዜን ማፋጠንና የስሜት ጤንነት ማሻሻልን ጨምሮ ጠንካራ ስነ-አእምሯዊ፣ ስሜታዊ እና አካላዊ ጥቅሞች አለው።

ምንጭ፡- ሣውና ፍሮም ፊንላንድ፣ ዘሄልዝ ሳይት፣ ቬሪ ዌል ማይንድ፣ ኤን ኤች አይ