የአዲስ አበባን አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን የቻሉ ተግባራዊ የጥናትና የምርምር ውጤቶች ቀረቡ

የአዲስ አበባ የዲሞክራሲ ስርዓተ ግንባታ ማስተባበሪያ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ከበደ ይመር

ሚያዚያ 5/2016 (አዲስ ዋልታ) ከ2010 እስከ 2015 ባሉት አምስት ዓመታት የመዲናዋን አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን የቻሉና ተቋማዊ ለውጦችን ያመጡ ተግባራዊ የጥናትና የምርምር ውጤቶች በአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ቀርቧል፡፡

3ኛው ከተማ አቀፍ የጥናትና ምርምር አውደ ጥናት “ችግር ፈቺ ምርምር ለአገራዊ ለውጥ እና ስኬት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል፡፡በመርሀ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ከ2010 እስከ 2015 ባሉት አምስት ዓመታት የሰራቸውን የጥናትና ምርምር ስራዎች አቅርቧል፡፡

በዚህም 39 የምርምር ስራዎች፣ 7 የማማከርና 6 የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተግባራትን ማከናወን የቻለ ሲሆን ከ23 ሴክተር መስሪያ ቤቶች በላይ መዳሰስ መቻሉ ተገልጿል፡፡

እነዚህ ጥናትና ምርምሮች በወረቀት ተሰንደው የተቀመጡ ብቻ ሳይሆኑ ተግባራዊ ለውጦች ማምጣት የቻሉ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን የአደረጃጀት ለውጥ ከማምጣት አንስቶ የተቋማትን ስያሜ እስከመቀየር የደረሰ መሆኑ ተነስቷል፡፡

ለአብነትም በቀድሞ ስያሜው ኢቨንስትመንት ኤጂንሲ የተሰኘው ተቋም ላይ ሰፊ ስራዎችን በመስራት የአደረጃጀት ለውጥ ከማምጣት አንስቶ ስያሜውንም ወደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መለወጥ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

በመሬት አስተዳደር በኩል የተገኙ ውጤቶች ሌላው ተግባራዊው ለውጥ ሲሆን በዚህም የግብር አወሳስንና የወሰን ማስከበር አገልግሎቶችን ከክፍለ ከተማ ወደ ወረዳ እንዲወርድ ማስቻሉ ተነግሯል፡፡ ይህም ለማኅበረሰቡ የሚቀርቡ አገልግሎቶችን ያቀለለ ሆኗል ተብሏል፡፡

የሙስና ተግባራት ሲሰሩበት የነበረው በመንግስታዊ ቢሮዎች በኩል በሚገዙ እቃዎች ላይም የተሰራው የጥናትና የምርምር ስራ ሌላው የሚጠቀስ ሲሆን ይህም ጥራታቸውን የሚቆጣጠርና ሙስናን ማስቀረት የቻሉ ስርዓቶች እንዲዘረጉ ማስቻሉ ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባሻገር የኢንስቱሪ ፓርኮች እንዲገነቡ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ ፣ ጥቃቅን አነስተኛ ንግድን ማስፋፋት፣ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ላይ የተሻሉ እድሎችን ማመቻት፣ ተቋማት የመረጃ አያያዝ ስርዓታቸውን እንዲያሻሽሉና ሌሎች በርካታ ተግባሮች እንዲከናወኑ ማገዙ ተጠቁሟል፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ የዲሞክራሲ ስርዓተ ግንባታ ማስተባበሪያ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ከበደ ይመር ፣ የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ደሳለኝ ጴጥሮስን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ሳሙኤል ሙሉጌታ (ከአዳማ)