የበዓሉ የኢድ ሶላት ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ የሚዘጉ መንገዶች ይፋ ሆኑ

ሚያዝያ 12/2015 (ዋልታ) 1444ኛው የኢድ አልፈጥር ረመዳን በዓል የኢድ ሶላት ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ለተሸከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች እንደሚኖሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር አሽከርካሪዎች ከዚህ በታች የተገለፁት መንገዶች ዝግ መሆናቸውን ተገንዝበው ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ አሳስቧል፡፡

በዚህም መሰረት፡-

– ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ ወደ ስታዲዮም የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር ኦሎምፒያ አደባባይ አከባቢ

– ከመገናኛ፣ በሃያ ሁለት ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድሃኒያለም፣ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ

– ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ባሻ ወልዴ ችሎት ወይም ፓርላማ መብራት

– ከፒያሣ አካባቢ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቸርችል ጎዳና ቴዎድሮስ አደባባይ

– ከተክለ ሀይማኖት በሜትሮሎጂ ወደ ስታዲዮም የሚወስደው መንገድ ሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት አካባቢ

– ከተክለ ሀይማኖት ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚወስደው መንገድ ጥቁር አንበሳ የኋላ በር አካባቢ

– ከሲኒማ ራስ በጎላ ሚካኤል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ጎላ ሚካኤል መስቀኛ

– ከጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ፣ ብሄራዊ ቲያትር የሚወስደው መንገድ ጎማ ቁጠባ

– ከባሻ ወልዴ ችሎት በኦርማ ጋራዥ ወደ ፍል ውሃ መስኪድ የሚወስደው መንገድ ንግድ ማተሚያ ቤት

– ከጎፋ በቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ ወደ ለገሐር አዲሱ መንገድ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ መስቀለኛው ላይ

– ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ሜክሲኮ አደባባይ

– ከሳሪስ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለቀላል መኪና የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ እንዲሁም ለከባድ መኪና አጎና ሲኒማ አካባቢ

ይለፍ ለሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከለሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፖሊስ የተሰጠውን መረጃ ተገንዝቦ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚጠቁሙት አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀም እና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ትዕዛዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ለእምነቱ ተከታዮች በሙሉ በዓሉ የፍቅርና የሰላም እንዲሆን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል መልካም ምኞቱንም ገልፆዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲዮም እና በዙሪያው የሚከናወነው የበዓሉ የኢድ ሶላት ላይ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የሚታደሙበት እንደመሆኑ የሶላት ስነ-ስርዓቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ እና የበአሉ ድባብ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ወቅታዊውን የፀጥታ ሁኔታ ያገናዘበ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል አስታውቋል፡፡

የዕምነቱ ተከታዮች እና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተለይም ለኢድ ሶላት የሚመጣውን ህዝበ ሙስሊም በማስተባበር እና የበዓሉን ድባብ ሊያደፈርስ የሚችል ችግር እንዳያጋጥም ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመስራት የሚያደርጉት ተሳትፎ የጎላ እንደሆነ የጠቀሰው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል በዘንድሮው በዓልም ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል ከዕምነቱ አባቶች እና ከወጣቶች ጋር ተገቢው ውይይት መደረጉን ገልጿል፡፡

የዕምነቱ ተከታዮች በየአካባቢያቸው በዓሉን ሲያከብሩም ሆነ ወደ ኢድ ሶላቱ ሲመጡ እንደወትሮው ሁሉ የፖሊስን መስተንግዶና ትዕዛዝ በማክበር ተባባሪ እንዲሆኑ እና የበዓሉ ስነ ስርዓት በሰላም እንዲጠናቀቅ መላው የከተማችን ነዋሪዎች የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሐይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በዚህ የፀጥታ ማስከበር ሂደት ውስጥ በአካባቢያችሁ ለሰላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮችን ስትመለከቱ በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲልም የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይሉ መልዕክቱን ያስተላልፋል።