ጠ/ሚ ዐቢይ ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ሚያዝያ 12/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለዒድ አል ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

የዘንድሮውን ዒድ አልፈጥር ስናከብር ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ በአንድነት ስለመቆምና ስለወንድማማችነት እያሰብን መሆን አለበት። የእስልምና አባቶች የዒድ ሶላትን በጀመዓ ስለመስገድ ተገቢነት ሲያስረዱ፣ “የአላህ (ሱ.ወ) እጅ ሰብሰብ ባሉ ሰዎች መሐል ይገኛል” የሚለውን የእምነቱን አስተምህሮ ይጠቅሳሉ፡፡ በነጠላ ከመስገድ በላይ ሰብሰብ ብሎ አብሮ መስገድ ከፍ ያለ ምንዳ ከማስገኘቱ በተጨማሪ የወንድማማችነት ስሜት ያጠናክራል፤ ጠላት ሸይጧንንም መግቢያ ቀዳዳ ያሳጣል። በዚህም ምክንያት ሕዝበ ሙስሊሙ በስግደት ወቅት አቅሙ በፈቀደ ሰብሰብ ማለትን፣ በጋራ መስገድን ይመርጣል።

በአንድነትና በጋራ መቆም የሚጠቅመው ለጸሎት ብቻ አይደለም። እንደ ሀገር የሚገጥሙ ፈተናዎችን በድል ለመሻገርም አብሮ መቆም ያስፈልጋል። በተለይ በዚህ ወቅት እኛ ኢትዮጵያውያን ከምን ጊዜው በላይ አንድነትን አጠንክረን የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን። ሀገራችን ሽግግር ላይ ናት። ከጉስቁልና ወደ ብልጽግና ለመሻገር ከአያሌ ዕንቅፋቶች ጋር የሞት ሽረት ትግል እያደረገች ነው። ትግሉን በአሸናፊነት ለመወጣት እኛ ልጆችዋ በየትግል መስኩ የድክመቶቻችንን ቀዳዳ ለመድፈንና ከችግሮቻችን በላይ ለመሆን ተግባብተን በጋራ መቆይ ይኖርብናል። ወደ ከፍታው መውጣት የምንችለው በመጓተት ሳይሆን በመደጋገፍ፣ በንትርክ ሳይሆን በሰከነ መልኩ በመመካከር ነው።

በነቢዩ ዘመን ገናና የነበርን ሕዝቦች ዛሬ የኋላቀርነትን ካባ ስንለብስ ያሳዝናል። ለነቢዩ ዘመዶችና ተከታዮቻቸው መጠለያና መሸሸጊያ የሆንን ሕዝቦች ዛሬ የገዛ ወንድም እኅቶቻችንን ከየመንደሮቻችን ለማስወጣት እጃችን ሲነሣ ደስ አይልም፤ ስለ ሐቅና እውነተኛነታችን የተመሰከረልን ሕዝቦች አንደበታችን ለቅጥፈት መከፈቱ፤ ጆሯችን በፕሮፓጋንዳ ወሬ መፈታቱ ያስተዛዝባል። እንዲህ ያሉት እኩይ ጠባዮች አይጠቅሙንምና ዛሬውኑ አሽቀንጥረን እንጣላቸው፤ ወደ ከፍታችን የሚመልሱንን መልካም ባህርያትን ለመላበስም ከአሁኑ መትጋት እንጀምር።

የሮመዳን ወር የፈጣሪን ሰላም፣ እዝነትና በረከት ተጠይቆ የሚገኝበት ወር እንደሆነ የእምነቱ አስተምህሮ ያስረዳል። በዚህ የጾምና የበረከት ወር የተገኘውንም ስንቅ ሕዝበ ሙስሊሙ ከዒዱ እለት አንሥቶ እስከ ቀጣዩ የሮመዳን ወር ድረስ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ውስጥ እየተረጎመው ይቆያል ተብሎ ይታመናል። ሰላም፣ እዝነትና በረከት ደግሞ ለሰው ልጆች የሕይወት ጉዞ እጅግ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ሰላም ኑሮን ያጣፍጣል፤ እዝነት የእርስ በርስ ግንኙነትን የሠመረ ያደርጋል፤ በረከት ደግሞ የኑሮን ጉድለት ይሞላል። ይኽ እንዲሆን ግን ከምንም በላይ ሦስቱን ጸጋዎችን መቀበል የሚያስችል ዝግጁ የሆነ ልብ ያስፈልጋል።

ሰላም ለሰላም የተዘጋጁ ብቻ ሳይሆን ለሰላም ዋጋ የሚከፍሉ ሰዎችን ይፈልጋል።  ጦርነት እንኳን ለሰላም ሲባል የሚደረግና ለጠብ ጫሪነት ሲባል የሚደረግ በሚል በሁለት ይከፈላል። ለሰላም የሚደረግ ጦርነት ዓላማው የሰላም ዕንቅፋቶችን ማስወገድና ሰላም የሚበቅልበትን ምድር ማስተካከል ነው። ለጠብ ጫሪነት የሚደረግ ጦርነት ግን ዓላማው የበለጠ ጠብንና ግጭትን ማባባስ ነው። ሰላም የጦርነት ማብቃት ወይም አለመኖር ብቻ አይደለም። ሰላም ከጦርነት በመለስ በሆኑ ጉዳዮች ሊደፈርስ ይችላል፤ ሰላም የልቡና መስማማትን፣ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖርን እና ከፈጣሪ ጋር ታርቆ መኖርን ይጠይቃል። እነዚህ ሦስቱ ተሟልተው ባልተገኙበት ሁኔታ ሰላም አይጸናም። የሮመዳን ወርና የዒድ አልፈጥር በዓል የሚያስገኙልን እነዚህን ሦስቱን የሰላም አላባዎችን ነው። በዕለት ተእለት ሕይወታችን ትግልና ጥረታችን እነዚህን ሦስቱን ለማስገኘት የሚችል መሆኑን ርግጠኞች መሆን አለብን። ሰላም ከጦርነት በላይ ጀግና ይፈልጋል የሚባለው ያለ ምክንያት አይደለም። ጦርነት በሌላው ላይ በሚኖር የበላይነት ይደመደማል፤ ሰላም የሚሰፍነው ግን በራስ ላይ በሚኖር የበላይነት ነው።

እዝነት የሰው ልጆችን እርስ በርሳቸው ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮም ጋር ተግባብተው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው ነው። እዝነት ከራስ ቆርሶ ለሌላው መስጠትን የሚጠይቅ ነው። እዝነት ለሌሎች ማዘን፣ መራራትና መጨነቅ ነው። የሰው ልጆች የዓለምን ተድላና መከራ በልካቸው ተካፍለው፣ ጉድለትን ሞልተውና ድካምን አበርትተው መኖር የሚችሉት እዝነት በዓለም ሲሰፍን ብቻ ነው። እዝነት በሌለበት ስግብግብነት፣ ጭካኔና ራስ ወዳድነት ይሰፍናሉ። ሌብነት፣ ዋልጌነት፣ ጥላቻ፣ ግጭትና ጦርነት የእዝነት አለመኖር የሚያበቅላቸው አረሞች ናቸው።

በረከት የሁለቱ ትሩፋት ነው። ለሰላማውያን ሰዎች፣ እዝነት ገንዘባቸው ለሆኑ ሰዎች በረከት የእነርሱ ናት። በረከት ግን የሰዎችን ዝግጅት ትፈልጋለች። የሚሠሩ እጆችን፣ የሚታረቁ ልቦችን፣ የሚታገሉ ክንዶችን፣ ላብ የሚያፈስሱ ጉልበቶችን፣ የሚጨነቁ ጭንቅላቶችን፣ የሚፍጨረጨሩ እግሮችን፣ የሚፈለፍሉ ጣቶችን፣ የሚማትሩ ዓይኖችን፣ የሚያዳምጡ ጆሮዎችን ይፈልጋል።

ወጥተንና ወርደን መሬቱን ካላዘጋጀነው ዝናቡ ምን ይጠቅማል? መስኖ ጠልፈን ካላመረትንበት፣ ግድብ ገንብተን ኤሌክትሪክ ካላመነጨንበት የውኃ ማማነታችን ትርጉሙ ምኑ ላይ ነው? ፈትነን መርምረን ማዕድኑን ካላወጣነው ምድሩ ምን ይሠራል? በግብርናና በኢንዱስትሪ ምርት ሀገሩን ካላጥለቀለቅነው 120 ሚልዮን ሕዝብ መያዝ ምን ያተርፋል? ተወዳዳሪና ተመራጭ ምርት አምርተን ካልሸጥንበት በአፍሪካ ቀንድ መኖር ምን ይፈይዳል አልምተንና አውጥተን ለቱሪዝም ካላዋልነው ቅርስ፣ ታሪክ፣ ባህልና መልክአ ምድር ከዘፈን በቀር ለምን ይጠቅማል?

የፈጣሪ በረከት የሚሠሩ እጆችን ነው የምትጎበኛቸው። በዜሮ ላይ ተጨምራ አታውቅም። ከሰነፎች ጋር ተገኝታ አታውቅም። ከታካቾች ጋር ውላ አታውቅም። ፈጣሪ የሰማዩንም የገጸ ምድሩንም፣ የከርሰ ምድሩንም ሀብት አትረፍርፎልናል። በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የሚፈስሱ ወንዞችን እንደ መቀነት አስታጥቆናል። አራቱንም የአየር ንብረቶች አጎናጽፎናል። ከርሰ ምድሩን በማዕድናት ሞልቶታል። ገጸ ምድሩን በዕጽዋትና በአትክልት ዓይነት አሸብርቆታል።

እንግዲህ የቀረ ነገር ቢኖር የእኛ ተግባብቶና ተስማምቶ መኖር ነው። ከትናንት ይልቅ ነገን፣ ካለፈው ይልቅ ዛሬን ተስፋ አድርጎ መነሣት ነው። የፈጣሪ በረከት እንዳንጠቀም የሚጋረጡብንን ፈተናዎች ለማሸነፍ ቆርጠን መነሣት አለብን። ፈተናዎቻችን የሚሸነፉት ዐቅማችንን ዐውቀን ራሳችንን መግዛት በቻልንበት ልክ ነው፤ ለዚህም ጾሙ  ያቆናጸፈንን ዐቅምና ልምድ ልንጠቀምበት እንችላለን። ከፀሐይ መውጣት እስከ ፀሐይ መግባት መጾም ራስን የመግዛት ውጤት ነው፤ የሚያጓጉና የሚያባብሉ ነገሮችን ለዓላማ ሲሉ እምቢ የማለት ውጤት፤ ስሜትን የማሸነፍ ውጤት። ነገሮች ወደሚወስዱን ሳይሆን እኛ ልንሄድበት ወደምንፈልገው መንገድ ለመጓዝ የመወሰን ዐቅም ነው። ይኼንን ዐቅም ወደ ብልጽግና ለምናደርገው ሽግግር ትልቅ ግብዓት አድርገን ልንጠቀመው እንችላለን። እኛ ሀገር አለን። ሀገራችን ሰው እንዲኖራት እናድርግ። ኃላፊነት በማይወስዱ፣ የት እንዳሉ በማይታወቁ፣ እንጀራ ሲጋገር በማይኖሩ፣ እንጀራ ሲበላ ግን ሌላውን ሁሉ ገፍተው እጃቸውን በሚዘረጉ፣ ከጤናችን ሳይሆን ከቁስላችን በሚያትርፉ፣ ከወዳጅ ይልቅ ጠላት ለመፍጠር በተሰለፉ ኃይሎች አንመራ። የእነርሱ ዓላማቸው ሰላምን፣ እዝነትንና በረከትን ከሀገራችን ማጥፋት ነውና።

ሀገራችንን የሚያጸኗት ሰላም፣ እዝነትና በረከት ናቸው። ሰላም ህልውናዋን ያጸናዋል። እዝነት ሕዝቦቿ ተከባብረው፣ ተፈቃቅደው፣ ተስማምተውና ተቻችለው እንዲኖሩ ያደርጋሉ። ለሰላም፣ ለእዝነትና ለበረከት ብቻ እጆቻችንን እንድንዘረጋና ልቦቻችንን እንድንከፍት አደራ እያልኩ በድጋሚ መልካም የዒድ አል ፈጥር በዓል እንዲሆን እመኛለሁ።

ዒድ ሙባረክ!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዚያ 2015 ዓ.ም