የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለአልሚ ባለሀብቶች ቦታ አዘጋጅቶ እየተጠባበቀ መሆኑን አስታወቀ

 

የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ

የካቲት 10/2013 (ዋልታ) – ቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው ተጠናቅቆ ጥር 30/2013 ዓ.ም በመመረቅ አምራች ባለሀብቶችን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

ፓርኩ ለሥራዉ ስኬታማነት የሚውሉ መሠረተ ልማቶችን ማሟላቱንና ባለሀብቶች በሚያቀርቡት መነሻ ፕሮጀክት መሠረት 142 ሄክታር የተዘጋጀ መሆኑን የአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የዕቅድ ዝግጅት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ በልስቲ ወርቁ ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው እንዲያለሙ የትውውቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የቡሬ የኢንዱስትሪ ፓርክ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ሰባት የገጠር ሽግግር ማዕከላት በመገንባት ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ በልስቲ ከእነዚህ ማዕከላት ውስጥ የሞጣ የሽግግር ማዕከል ግንባታ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ቀሪዎቹ የገጠር ሽግግር ማዕከላትም በያዝነው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚገመት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከማኅበራት፣ ከአርሶ አደሮች፣ ከምርት ማሰባሰቢ ማዕከላትና ከዩኒዬኖች ለፓርኩ የሚውሉ ዋና ዋና ግብዓቶች (ምርት ማሰባሰብ) ሥራ በመሠራት ላይ እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ይህን ለማሳካት የግብርናና ሌሎች ተቋማት ከፓርኩ ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ የተቀመጠ አቅጣጫ መኖሩን ነው አቶ በልስቲ ያስረዱት፡፡ በዚህ መሠረት ሪችላንድ ባዮ ኬሚካል ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ምርትን በማሰባሰብ ወደ ትግበራ ሙከራ መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡
(ምንጭ፡- አብመድ)