የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ40 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊዘረጋለት ነው

በአማራ ክልል የተገነባው ቡሬ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ40 ሚሊየን ዶላር በላይ በሚገመት ወጪ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር እንደሚዘረጋለት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የቡሬ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቅርቡ ለምረቃ የሚበቃ ሲሆን፣ ከግንባታው ጋር የታቀደ የኤሌክትሪክ ሃይል መሰረተ ልማት እንዳልነበረው ተገልጿል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን፣ የፌዴራል መንግስት ለፓርኩ ኃይል ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ከ80 እስከ 160 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስፈልግ በጥናት መለየቱንም ገልጸዋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ ለሚጀምሩ ፋብሪካዎች ከአካባቢው ሀይል ማድረስ የሚያስችል አቅም እንደሌለም ተናግረዋል።

በመሆኑም ከባህርዳርና ከደብረማርቆስ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም ለቡሬ ሁለት አማራጭ ቀርቦ ሲጠና መቆየቱን የገለጹት አቶ ሞገስ፣ ከደብረማርቆስ ቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያና ንዑስ ሀይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከዋጋም አንጻር አዋጭ ሆኖ በመገኘቱ ተመራጭ መሆኑን አስረድተዋል።

92 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ግምታዊ ዋጋ 40 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ “ስራው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል” ብለዋል።