139 በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ የቀበሌ ቤቶችን ለችግር ለተጋለጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ተላለፉ

ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በአራዳ ክፍለ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 139 የቀበሌ ቤቶችን በማስለቀቅ ለአቅመ ደካሞች፣ ረዳት ለሌላቸው እና ለአካል ጉዳተኞች በዛሬው ዕለት አስረክበዋል፡፡

የቀበሌ ቤቶቹን በማስተላለፍ መርሐግብር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት በከተማ ህገወጥነትን በመከላከል እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ስርዓትን ለማስፈን የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በአራዳ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ 139 አባወራዎች እና አካል ጉዳተኞች የተላለፉት የቀበሌ መኖሪያ ቤት የፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንዱ ማሳያ መሆናቸውን ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በቅርቡ በማጥራት ስራ የተለዩ እና በተለያዩ አካላት በህገወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚከፋፈሉ ምክትል ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡

የቀበሌ መኖሪያ ቤት ተጠጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በቤት ዕጦት ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸው በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቤት ባለቤት በመሆናቸው መደሰታቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሬ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡