የቢሾፍቱ ሰንዳፋ አስፋልት ኮንክሬት የመንገድ የግንባታ 19 በመቶ መድረሱ ተገለጸ

የቢሾፍቱ ሰንዳፋ አስፋልት ኮንክሬት የመንገድ የግንባታ

ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – የቢሾፍቱ ሰንዳፋ አንደኛ ደረጃ አስፋልት ኮንክሬት የመንገድ የግንባታ ሂደቱ 19 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።

55 ኪሎሜትር የሚሸፍነው የቢሾፍቱ ሰንዳፋ አስፋልት ግንባታ ሶስት አመት ጊዜ የተያዘለት ሲሆን፣ 915 ሚሊየን ብር በጀት ተይዞለት ግንባታው እየተካሄደ እንደሆነና ዲዛይኑ የተሰራው ግንባታውን በሚያከናውነው ሀገር በቀል ተቋራጭ መሆኑ ተገልጿል።

የመንገዱን ዲዛይን ሠርቶ በማጸደቅና አሁን በደረሰበት 19 በመቶ የግንባታ ሂደት አንድ አመት ተኩል የወሰደ ሲሆን፣ በቀሪው አንድ አመት ተኩል ግባታውን ለማጠናቀቅ ይሠራል ተብሏል።

በሚቀጥለው አመት አስፋልት የማልበስ ስራ እንደሚጀመርና መንገዱ ሲጠናቀቅ አሁን ላይ በጠጠር መንገዱ ከቢሾፍቱ ሰንዳፋ ለመድረስ የሚወስደውን የሁለት ሰዓት ጊዜ ወደ 45 ደቂቃ እንደሚያወርደው ተገልጿል።

መንገዱ ከአዲስ አበባ ጅቡቲና ከአዲስ አበባ መቀሌ የሚደረገውን የተሽከርካሪ ጉዞ በአዲስ አበባ መዞርን የሚያስቀርና በደብረ ብርሃን በኩል የሚያሳልጥ መሆኑም ተጠቁሟል።

የመንገዱ ግንባታ የብዙ አመታት የአካባቢው ማህበረሰብ ጥያቄ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ በአካባቢ ያለውን የግብርና ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ ማድረስ እንደሚቻል ነው የተነገረው።

ለመንገዱ ግንባታ ሂደት ማህበረሰቡ ከፍተኛ እገዛ አያደረገ በመሆኑ የወሰን ማስከበር ስራውን ላይ ያለምንም ችግር በማከናወን የካሳ ክፍያ ሳይፈጸምላቸው ሁሉ ወደ ግንባታ እንዲገባ ማድረጉ ተመላክቷል። አሁን ላይ የካሳ ክፍያው መከናወኑም ተገልጿል።

(በምንይሉ ደስይበሉ)