የቤንዚን፣ ናፍጣ እና ኬሮሲን የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ባለበት ይቀጥላል ተባለ

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም የቤንዚን፣ ናፍጣ እና ኬሮሲን (ነጭ ጋዝ) የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በግንቦት ወር ሲሸጥበት በነበረው እንደሚቀጥል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የተጠቀሱት ምርቶች መሸጫ ዋጋ በዓለም ገበያ ቢጨምርም መንግሥት የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ለማስቻል የምርቶቹ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ያለምንም ለውጥ ባለበት እንዲቀጥል መወሰኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ነገር ግን የአውሮፕላን ነዳጅ፣ የቀላል ጥቁር ናፍጣ እና የከባድ ጥቁር ናፍጣ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በዓለም ዐቀፍ ዋጋ ተሰልቶ የመጣው ልዩነት ሙሉ በሙሉ ወደ ተጠቃሚው እንዲተላለፍ መወሰኑን ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።