ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) ከውጭ አገር ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።
ኮርፖሬሽኑ ለ2014/15 የሰብል ምርት ዘመን 12 ሚሊዮን 876 ሺሕ 623 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ገዝቻለው ብሏል።
ከዚህ ውስጥ ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ 9 ሚሊዮን 829 ሺሕ 190 ኩንታል የአፈር የተለያዩ ማዳበሪያ አይነቶች ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን ገልጿል።
ከዚህም 8 ሚሊዮን 243 ሺሕ 689 (84 በመቶው) ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጋሻው አይችሉህም ተናግረዋል።
ለዘንድሮ የሰብል ዘመን ከሞሮኮው የአፈር ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ኦ ሲ ፒ (OCP) የተገዛው የ ኤን ፒ ኤስ (NPS) አይነት ማዳበሪያ ወደ ጅቡቲ ወደብ የማጓጓዝ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ከውጭ ሀገር ከተገዛው 5 ሚሊዮን 1 ሺሕ 100 ኩንታል ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ በአራት ዙር ጅቡቲ ወደብ የተራገፈው የዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ መጠን 1 ሚሊዮን 953 ሺሕ 670 ኩንታል (39 በመቶ) ደርሷል ነው ያሉት።
ከሁለት ቀን በኋላ ተጨማሪ 450 ሺሕ ኩንታል ዩሪያ ወደብ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አብራርተዋል።