የብሄራዊ ህብረተሰብ ተኮር ምክክር እና ወጣቶችን ያማከለ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እየሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ

                                                   የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ከሚል

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ከሚል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሚኒስቴሩ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት አመታት ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ በሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የብሄራዊ ህብረተሰብ ተኮር ምክክር እና ወጣቶችን ያማከለ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ጥናት አድርገን እየሰራን እንገኛለን ያሉት ሚኒስትሯ፣ የምክክር መድረኩ በማህበረሰብ እንዲሁም በሊህቃን ደረጃ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ውይይቱ ከቀበሌ እና ጎጥ ጀምሮ ማህበረሰቡን በማካተት የሚካሄድ ሲሆን፣ በልሂቃኑ ዘርፍ ደግሞ የፓለቲካ ፓርቲዋች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ፓለቲከኞች፣ የታሪክ ምሁራን እና ሌሎች በየዘርፋ እየተሳተፉበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የገለጹት ወ/ሮ ሙፈሪሃት፣ ባሳለፍነው አመት ብቻ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተመርቀው የተመዘገቡ 116ሺህ ወጣቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በአስር ዮኒቨርስቲዋች ውስጥ የመጀመሪያው ዙር ስልጠና 35ሺህ ወጣቶችን በሶስት ዙር ለማሰልጠን እንቅስቃሴ መጀመሩንም አንስተዋል።

ለ45 ቀናት በሚቆየው በዚህ ስልጠና ወጣቶች በስነ ልቦና ውቅር፣ በስሜት ብስለት እንዲሁም በስራ የመፍጠር ባህል እንዲያዳብሩ የሚያግዝ ነው ተብሏል።

ወጣቶቹ ስልጠናቸውን ሲጨርሱ ለ10 ወራት በአገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች ተሰማርተው ልምድ በመቅሰም አዲስ ባህል እና ልምድን ያገኛሉ የተባለ ሲሆን፣ በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ወርደው ማህበረሰቡን እንደሚያገልግሉም ተገልጿል።

(በቁምነገር አህመድ)