“የብዙሃን እናት መጠጊያ የምንላት እማማ ናትና ሀገሬን አትንኳት”

ትውልድ እና እድገቱ በውብ ድምፅ ባዜመላት አዲስ አበባ ነው፡፡ አንጋፋው ድምጻዊ ጌታቸው ካሳ ሙዚቃን ማንጎራጎር የጀመረው ገና ታዳጊ እያለ ነበር፡፡

የሙዚቃ ፍቅሩ ግን በቤተሰቦቹ ዘንድ በተለይም በአባቱ ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ የአንጋፋው አርቲስት እውነተኛ ስም “ጌታቸው እሸቴ” ነበረ፡፡ ይህ አርቲስት በኪነ-ጥበቡ ተማርኮ ማንጎራጎር ሲጀምር አባቱ ድምጹን በሬድዮ ይሰሙታል፡፡ አባት “ልጅህ አዝማሪ ነው” መባላቸው ክብራቸውን የሚቀንስ ሆኖ ስለተሰማቸው ልጃቸውን ያስጠሩትና በቁጣ እንዲህ አሉት፤ “ከዛሬ በኋላ ከዘፈንክ ግንባርህን በጥይት እበሳዋለሁ”፡፡

ጌታቸው ግን ካደረበት የሙዚቃ ፍቅር የተነሳ ቁጣው አላስደነገጠውም እንዲያውም ከአባቱ እየተደበቀ ወደ ዘመኑ የምሽት መዝናኛ ክለቦች፣ ልዩ ልዩ መድረኮች ጎራ እያለ መዝፈኑን ቀጠለ፡፡

በዚህን ጊዜም በአንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ ዐይን ውስጥ ገባ፡፡ ጌታቸው ደስታም ወጣቱን በሬድዮ እንዲዘፍን ይጋብዘዋል፡፡ የድምፃዊው አባት ልጃቸው በሬድዮ እንደዘፈነ ቢሰሙ ሊገድሉት ይችላሉ በሚል ፍራቻ ሬድዮ ላይ ሲዘፍን ስሙን ቀይረው “ጌታቸው ካሳ” አሉት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተወዳጁ አርቲስት ጌታቸው ካሳ ተብሎ መጠራት ጀመረ፡፡

“እመኛለሁ” የተሰኘው ሙዚቃ የመጀመሪያ ስራው ነበር፡፡ ሙዚቃው በበርካቶች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ስለነበር ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ ጌታቸው የሚለው ስሙን ትተው እመኛለሁ እያሉ እስከመጥራት ደርሰዋል፡፡

አርቲስት ጌታቸው ፈጣን ባንድ፣ ዋቤ ሸበሌ ባንድ፣ ዋልያ ባንድ እና ሂልተን ባንድን ጨምሮ ከበርካታ ባንዶች ጋር ተጫውቷል።

በ15 ብር ደሞዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ አዲስ አበባ ውስጥ ታዋቂ ክለብ በሆነው በሶምብሪኖ አኮርዲዮን እየተጫወተ ሰርቷል፡፡

በመቀጠልም አክሱም ሆቴል ስራዎቹን ማቅረብ ጀመረ። ጌታቸው በፓትሪስ ሉሙምባ ክለብ፣ በቬኑስ ክለብ እና ጣይቱ ሆቴልም ተጫውቷል። በወቅቱ እጅግ ተወዳጅነትን ከማትረፉ የተነሳ እያንዳንዱ ክለብ እሱን ለመቅጠር ያናግረው ነበር፡፡

በ1983 በሀገረ አሜሪካ የመጀመሪያውን ሲዲ አሳተመ። ከ28 ዓመታት ከአሜሪካ የስደት ሀገር ኑሮ በኋላ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል፡፡

አንጋፋው አርቲስት ጌታቸው ካሳ ባደረበት ሕመም የህክምና እርደታ ሲደረግለት ቆይቶ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

ጌታቸው ካሳ ለህዝብ ካደረሳቸው በርካታ ስራዎች መካከል አዲስ አበባ፣ ትዝ ባለኝ ጊዜ፣ የከረመ ፍቅር፣ ሀገሬን አትንኳት፣ ብርቱካን ነሽ ሎሚ፣ ብቻየን ተክዤ የሚሉት እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡