የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲያንሰራራ የፋይናንስ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – በኮቪድ-19 ምክንያት የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲያንሰራራ የፋይናንስ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ገለጹ።

“የፋይናንስ ተቋማት ሚና ለቱሪዝም እድገት” በሚል መሪ ቃል የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት የሚያስችል የባለ ድርሻ አካላት ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ያለማቋረጥ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የሚገኝ ትልቅ ዘርፍ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሂሩት ካሳው፣ የቱሪዝም ልማት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በቱሪዝም ሃብቶች የታደሉ አገራት ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለስራ ፈጠራ፣ ለንግድ ሚዛን መመጣጠንና አገራዊ ገቢን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።

የቱሪዝም ዘርፉ በኢትዮጵያ የልማት እቅድ ተዘጋጅቶለት መመራት ከጀመረ ረዘም ያለ ጊዜ  ያስቆጠረ ቢሆንም፤ በታደልነው ፀጋ ልክ ተጠቃሚነታችንን ማረጋገጥ አልቻልንም ብለዋል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረትና የግል ዘርፉና ባለድርሻ አካላት እያደረጉ ባለው የተቀናጀ ጥረት ጉልህ መሻሻሎች ማሳየቱንም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

ዘርፉ በርካታ መልካም እድሎች ያሉት የመሆኑን ያህል በብዙ ተግዳሮቶች የተተበተበ በመሆኑ ማደግ ባለበት ደረጃ አላደገም ብለዋል።

በቱሪዝም ልማት ከሚስተዋሉ ቁልፍ ችግሮች መካከል ለዘርፉ የሚሰጡ የብድር አቅርቦቶችና ሌሎች የፋይናንስ ድጋፎች ዝቅተኛ መሆን ተጠቃሽ መሆኑን  ያስረዱት ሚኒስትሯ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲያንሰራራ ለማድረግ ልዩ የማነቃቂያ ፓኬጅ ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

(በነስረዲን ኑሩ)