የተባበሩት መንግሥታት ስጋት

መስከረም 7/2014 (ዋልታ) ባለፈው ሳምንት እርዳታ ጭነው መቀሌ ከደረሱ 149 ተሽከርካሪዎች ውስጥ የተመለሰ አንድም ተሽከርካሪ አለመኖሩ አሳሳቢ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ፡፡

ከባለፈው ሐምሌ ጀምሮም ወደ ክልሉ ከገቡ 466 እርዳታ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ውስጥ የተመለሱት 38ቱ ብቻ እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ የህይወት አድን ሰብኣዊ ድጋፍን እንዲያደርሱ ነው የምንፈልገውም ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ የሚገቡ እርዳታ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች እየተመለሱ አለመሆኑንና ይህም አሳሳቢ እንደሆነ በመጥቀስ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በአሸባሪው ሕወሓት ላይ ጫና እንዲያሳድር ቢጠይቅም ሰሚ ጠፍቶ ከርሟል፡፡ ይልቁንም ለሽብር ቡድኑ በመወገን እርዳታ አልደረሰም የሚለውን ፕሮፖጋንዳ ሲደግፉ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የሽብር ቡድኑ ግን እርዳታ ጭነው የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን በማስገደድ ታጣቂዎቹንና የሚዘርፈውን ንብረት እንዲያመላልሱ እያደረገ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ሲወጡ መሰንበታቸው ይታወሳል፡፡