የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውል 60 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለኢትዮጵያ አደረገች

ሐምሌ 12/2014 (ዋልታ) የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውል 60 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ለኢትዮጵያ አደረገች።

ድጋፉ በትግራይ፣አማራ እና አፋር ክልል አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚሹ ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ምላሽ ለመስጠት ነው ተብሏል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት ተከትሎ በትግራይ፣አማራ እና አፋር ክልል ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጾ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላደረገው ድጋፍ አመስግኗል፡፡

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ በክልሎቹ ለሚገኙ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎችን አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ለማከፋፈል ያግዛል ብሏል።

በኢትዮጵያ የሰሜኑ ጦርነት ፣ የኮቪድ-19 ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ እንዲሁም የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንዳስከተለ እና በዚህም የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ባለፉት 12 ወራት በእጥፍ ጨምሮ 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን መሆኑን አስታውቋል፡፡