የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሰራር የሀገሪቱን ዕዳ ዝቅ ማድረግ እንደቻለ ተገለፀ


ጥር 4/2015 (ዋልታ) ነዳጅ ከጅምላ ድጎማ ወጥቶ የታለመለት ድጎማን ተግባራዊ በማድረጉ በወር 15 ቢሊዮን ብር የነበረውን ዕዳ ወደ 3 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማድረግ መቻሉን የነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ባለስልጣኑ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶችን በከፍተኛ ዋጋ አስገብታ በዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ በማቅረቧ ለ187 ቢሊዮን ብር ዕዳ ዳርጓታል፡፡

በነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን የነዳጅ ውጤቶች የግብይት ስታንዳርድ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ለሜሳ ቱሉ ለዋልታ እንደገለጹት ከዚህ ችግር ለመውጣትና መንግስት የነዳጅ ዋጋን ለማረጋጋት ከጅምላ ድጎማ በመውጣት አነስተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ የታለመለት የነዳጅ ድጎማን አሰራር ተግባራዊ አድርጓል፡፡

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ መንግስት ባለፈው ዓመት ከመወሰኑ በፊት ኢትዮጵያ የነበረባት ዕዳ 70 ቢሊዮን ብር የነበር ሲሆን ዓለማቀፉ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት በወር 15 ቢሊዮን ብር ዕዳ ደርሶም እንደነበር ተገልጿል፡፡

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ በመደረጉ ከሰኔ 2014 ጀምሮ የእዳው መጠን ከ15 ቢሊዮን ብር ወደ 3 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ለ5 ዓመት የሚቆይ ሲሆን ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ከተስተካከለ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ከአቅም በላይ ሆኖ ማስፈጸም ካልተቻለ እንዲሁም መንግስት በቢሊዮን የሚቆጠር ወጪ እያወጣ ህብረተሰቡ ግን በአግባቡ ካልተገለገለ በጥናት ላይ ተመስርቶ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡

በተስፋዬ አባተ