ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከፈረንሳይና ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

ጥር 4/2015 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከፈረንሳይና ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያይተዋል።

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባኤርቦክ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪ ኮሎናን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል።

በዚህም የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጋር በነበራቸው ውይይት የሀገራቱን ረጅም ዘመን የዘለቀ ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሚደረገው መልሶ ግንባታ ተግባራት ሁለቱ ሀገራት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ሚኒስትሮቹ አረጋግጠዋል፡፡

የመልሶ ማቋቋምና የመደገፍ ስራዎች ሴቶችን ታሳቢ በማድረግ ላይ ያተኮሩ መሆን እንዳለባቸውም በውይይታቸው ተነስቷል።