የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የስራ አፈጻጸም ውይይት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቀቀ

ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ላለፉት ሶሰት ቀናት በመቀሌ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የስራ አፈጻጸም የውይይት መድረክ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ዛሬ ተጠናቀቀ።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሰራ አስፈጻሚ ዶክተር አብረሃም በላይ በተገኙበት የተካሄደው መድረክ ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፉት ጊዜያት ባከናወናቸው ስራዎች ዙሪያ ተወያይቷል።

በክልሉ የጸጥታ ሁኔታ፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሰብአዊ እርዳታና በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሳጣጥ እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ መከላከል ላይ ስለተከናወኑት ተግባራት በውይይቱ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።

ጊዚያዊ አስተዳደሩ በቀጣይ ወራት ትኩረት ሰጥቶ ስለሚያከናውናቸው ስራዎችም አቅጣጫዎች ተቀምጧል።

በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ትምህርት፣ ጤና ፣ ግብርናና ሌሎችም የሰራ ዘርፎች ወደነበሩበት ለመመለስ በመድረኩ ተሳታፊዎች የጋራ መግባባት ላይ ተደርሳል።

በተለይም መደበኛ ትምህርትን የተገኘውን አማራጭ ሁሉ በመጠቀም ለማስጀመር፤ በጤናው ዘርፍም ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አገልግሎቱን ለማጠናከርም እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የቢሮ ኃላፊዎችና የዞን አመራሮች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።