የቻይና ዩዋን ዓለም አቀፍ መገበያያነቱ እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

ሚያዝያ 20/2015 (ዋልታ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቻይና መገበያያ ገንዘብ ዩዋን በይፋዊ ስሙ ረምንቢ በአንዳንድ አገራት የዶላርን ሚና በመተካት ለዓለም አቀፍ ግብይት እየዋለ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

ከሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ ሩሲያ ከዓለም አቀፍ የክፍያ ስርዓት ከሆነው ስዊፍት መታገድን ተከትሎ አማራጭ የክፍያ ስርዓት አስፈላጊነት ለብዙ አገራት ግልፅ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ለዚህም ይመስላል በርካታ አገራት በቻይናው ዩዋን ለመገበያዬት ፈቃደኝነት ከማሳየትም አልፎ ተግባራዊ ግብይት እየፈጸሙ የሚገኙት፡፡

እስከ አሁን አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ በርካታ ነዳጅ ላኪ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከቻይና ጋር በዩዋን መገበያዬት  ከጀመሩ ሰንብቷል ተብሏል፡፡

እነዚህ አገራት ደግሞ በፍጥነት እያደጉ ያሉ እና የብሪክስ አባል አገራት እና በቅርብ አባል ለመሆን ያመለከቱ ናቸው፡፡

በሆንኮንግ የኢነቨስትመንት ስትራቴጅስቱ ቺ ሎ  “የዓለም ከፍተኛ ሸቀጥ ላኪ እና አስመጭዎቹ ቻይና፣ ሩሲያ እና ብራዚል ለድንበር ዘለል ግብይት ዩዋንን ለመጠቀም እየሰሩ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ይህ የአገሮቹ ትብብር በግዜ ሂደት ሌሎች አገሮችም ዩዋንን ለዓለም አቀፍ ክፍያ ለመጠቀም እንዲያስቡ ያደርጋል”ብለዋል፡፡

ለምሳሌ በቻይናው ገንዘብ ግብይት ከሚካሄድባቸው አገራት አንዷ ሩሲያ በዓመቱ መጀመሪያ አንድ በመቶ የነበረው የግብይት መጠን ወደ 45 በመቶ ከፍ ብሏል ይላል የሬውተርስ ዘገባ፡፡ ይህ ከቻይና ውጭ በዩዋን ክፍያ ከሚፈጸምባቸው አገራት በትልቅነቱ አራተኛው ማዕከል ያደርገዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ዩዋን ስዊፍት (swift system) በተባለው የዓለም አቀፍ  የክፍያ ስርዓት ውስጥ 1.3 ከመቶ ድረሻ የነበረው ሲሆን እ.ኤ.አ በየካቲት 2023 ወደ 4.5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ታውቋል፡፡

ቁጥሩ ከዚህ በበለጠ ፍጥነት ሊጨምር እንደሚችልም ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሩሲያ-ዩክሬይን ጦርነትን ተከትሎ የምዕራቡ ዓለም በሌሎች አገራት ላይ ልዩ ልዩ ጫናዎች ማድረጋቸው እና ማዕቀብ መጣላቸው ነው ተብሏል፡፡

ዩዋን በዓለም አቀፍ የግብይት ስርዓት ውስጥ ዶላርን ባይተካ እንኳን ለቻይና ዘርፈ ብዙ ብሄራዊ ጠቀሜታዎችን ያስገኝላታል፡፡ለአገሪቱ ገንዘብ ምንዛሪ መዋዠቅን ይገታላታል እንዲሁም በአሜሪካ ከሚደርስባት የማዕቀብ ጉዳት ተጋላጭነትን ይቀንስላታል ተብሏል፡፡

በዚህም ሆነ በዚያ የቻይናው ዩዋን ዶላር በብቸኝነት ተቆጣጥሮት የነበረውን የዓለም አቀፍ የግብይት ስርዓት ውስጥ ሚናው እጨመረ መጥቷል፡፡ እድገቱ የመጣው የዩዋን ዓለም አቀፋዊ ደረጃ በዓለም ሁለተኛ ትልቁ ኢኮኖሚ መጠናከር እና ተፅዕኖ ላይ የተመሰረተ መሆኑም ነው የተነገረው::