ጤና ደጉ – የጸጉር መነቃቀል ችግር


በተለያዩ ምክንያቶች የጸጉር መነቃቀልና መርገፍ ችግር ያጋጥማል። በየቀኑ ከ50 እስከ 100 ጸጉሮች መርገፍ የተለመደ ሁኔታ ነው። ይህ ብዙ የሚያሳስብ አይደለም።

መጠኑ ከላይ ከተጠቀሰው በላይ ከሆነ ግን በህክምና አጠራር ቴሎጂን ኢፍሉቪየም (telogen effluvium) የተባለ የጸጉር መነቃቀልና መሳሳት ችግር አጋጥሟል ማለት ነው። ለዚህ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ወደ ሃኪም መሄድ ያስፈልጋል።

የጸጉር መነቃቀል መንስዔዎች

ሀ. የሆርሞን መለዋወጥ፦ ለምሳሌ የታይሮይድ ሆርሞን መጠን መለዋወጥና ያለመመጣጠን ጊዜያዊ የሆነ የፀጉር መነቃቀል እና መሳሳት ችግር ሊያስከስት ይችላል፡፡ ለምሳሌ በእርግዝና ወቅት፣ ጡት በማጥባት ወቅትና ሴቶች በሚያርጡበት ወቅት ሊከሰት የሚችል ነው።

ለ. የጭንቅላት ኢንፌክሽን፡- እንደ ጭርት፣ ፎሮፎር፣ ቆረቆር እና የመሳሰሉት እንፌክሽኖች በጭንቅላት፣ ፀጉርና ቆዳ ላይ በመውጣት ፀጉር እንዲነቃቀል የሚያደርጉ ሲሆን በአንዳንድ ቦታ ላይም ፀጉር እንዲመለጥ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ሐ. ሌሎች መንስኤዎች፦ በጭንቀት፣ በድብርት፣ በልብ ችግር፣ በደም ማነስ እና ግፊት ምክንያቶች አልያም እነዚህን ለመከላከል በሚወሰዱ መድኃኒቶች የተነሳ የጸጉር መርገፍ ሊከሰት ይችላል፡፡

መ. ለወሊድ መከላከያነት የሚወሰዱ መድኃኒቶች የጸጉር መነቃቀልና መሳሳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ሠ. የዕድሜ መግፋት እና የስኳር ህመምም በተመሳሳይ የፀጉር መሳሳት ችግርን ሊያስከትል ይችላል።

ረ. የካንሰር ህክምና፦ ለካንሰር ህመም የሚወሰዱ አንዳንድ መድኃኒቶች ለጸጉር መነቃቀልና መሳሳት ያጋልጣሉ።

ሰ. ከፍተኛ የሆነ የክብደት መቀነስ፦ በአንድ ጊዜ ከ10 ኪሎ ግራም በላይ ክብደታችን ድንገት ሲቀንስ የፀጉር መነቃቀልን ያስከትላል።

ሸ. የአይረን ማዕድን እጥረት፡- የቫይታሚን ኤ እጥረት የጸጉር መሳሳትና መመለጥ ሊያስከትል ይችላል። መጠኑን አብዝቶ ከተወሰደም የፀጉር መሳሳትንም ሆነ መመለጥን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያፋጥን ይችላል ነው ያለው የአሜሪካ የቆዳ እና ፀጉር ህክምና ማህበር።

የጸጉር መነቃቀል መፍትሄዎች

አንዳንድ የጸጉር መርገፍ ምክንያቶች ጊዜያዊ ስለሚሆኑ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሊስተካከል የሚችል ችግር ነው። በተለይ ምክንያቶቹ ከህክምና ጋር የተያያዙ ከሆኑ፣ ጸጉር ተመልሶ ያድጋል። በሌላ በኩል ከዕድሜ ጋር የተያያዘ ከሆነ ተፈጥሯዊ ክስተት በመሆኑ ላይመለስ ይችላል።

የጸጉር መርገፍና መሳሳቱ መንስኤ ከጭንቀት ጋር የተያያዘ ከሆነ ሊወሰዱ የሚችሉ መድኃኒቶች ስላሉ ሀኪም ማማከር ጠቃሚ ነው። የእንግሊዙ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (NHS) እንደሚጠቁመው አንዳንድ መድኃኒቶች ለወንድና ለሴት ብቻ ተብለው የተዘጋጁ ሲሆን ፊናስተሪድ እና ሚኖክሲዲል ለዚህ ጥሩ ምስሌ ናቸው።

ፊናስተሪድ ለወንዶች የሚሰጥ ሲሆን ሚኖክሲዲል ደግሞ ለሴቶች የሚታዘዝ የጸጉርን መነቃቀል የሚቀንሱ መድኃኒቶች መሆናቸው ነው የተገለጸው።

በራስ ቅል ላይ በፈንገስ የሚከሰቱ ቁስሎች ካሉ ተገቢ ህክምና ማድረግ፣ ከሕክምና ጎን ለጎን የተመጣጠኑ ምግቦችን መመገብ ጤናማ የፀጉር ዕድገት ዑደት እንዲኖር ይረዳል። ለጤናማ የጸጉር ዕድገት እንደ ፕሮቲን፣ በፍራፍሬ የበለፀጉ ምግቦች፣ ዚንክና ማዕድናትን የያዙ ምግቦችን መመገብ በጣም ጠቃሚ ነው።

ምንጭ፡- National Health Service (NHS) እና American Academy of Dermatology Association (AADA)

በቴዎድሮስ ሳህለ