የአልሲሲ ንግግር ኢትዮጵያ 2ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት የምታደርግበት ቀን መቃረቡን ተከትሎ ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው- ረ/ፕሮፌሰር አደም ካሚል

ረ/ፕሮፌሰር አደም ካሚል

መጋቢት 22/2013 (ዋልታ) – የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ ንግግር ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለማድረግ ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ ጫና ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ገለጹ፡፡

የግብፁፕሬዝዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ከሰሞኑ የህዳሴው ግድብ ግንባታን በተመለከተ ማስፈራሪያ ያዘለ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ከዓባይ ወንዝ ላይ የግብፅን ድርሻ መንካት ቀጠናውን የሚያናጋ ነው ብለዋል፡፡ “አሁንም ደግሜ ልናገር እፈልጋለው ከግብፅ የውሃ ድርሻ አንድ ጠብታ እንኳን ቢሆን ማንም ሊወስድ አችልም” ሲል ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በትላንትናው እለት በሲውዝ ካናል ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግብፅ እና የአረቡ ዓለም ታሪክ እና ፖለቲካ አጥኚ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል የፕሬዝዳንት አልሲሲ ንግግር አዲስ አይደለም ወትሮም የተለመደ ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ለማድረግ ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ ጫና ለመፍጠር ያለመ ንግግር መሆኑን  የጠቀሱት ምሁሩ፣ የሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል ግብፃዊያን የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን የውስጥ አንድነት ማናጋት ዋንኛ ስትራቴጂያቸው አድርገው በትኩረት እየሰሩበት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ሱዳንንም በመያዝ ሎሎችንም የአረቡን ዓለም ሀገራትን ከጎናቸው ለማሰለፍ እየጣሩ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል፣ ኢትዮጵያ በእስልምናው ዓለም ያላትን ተቀባይነት በመጠቀም የተከፈተባትን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ አፀፋዊ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በመስራት መመከት እንዳለባት አሳስበዋል፡፡

ግብፆች ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትፈጠር በፍጹም አይፈልጉም ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኖረ አንድነቱን እና መቻቻል ባህሉን በማጠናከር ግብፅ የኢትዮጵያ አንድነት ለማናጋት የያዘችውን እስትራቴጂ ሊያከሽፉ ይገባል ብለዋል፡፡

በህብረተሰቡ ጠንካራ ድጋፍ የተጀመረው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስ አሁንም ቢሆን ድጋፋቸወን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

(በአሳየናቸው ክፍሌ)