ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሆን መንግሥት ለባለድርሻ አካላት ድጋፍ ያደርጋል – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

መጋቢት 22/2013 (ዋልታ) – ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ተአማኒ መሆን እንዲችልና ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በተገቢው መልኩ እንዲወጡ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ ብሔራዊ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ፡፡

የአዲስ ወግ ውይይት ሐሰተኛ መረጃ በሰላማዊ ምርጫ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ መግታት በሚቻልበት አግባብ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት አቶ ገዱ ከልዩ ልዩ የመንግሥት አካላት የተውጣጣ ሀገር አቀፍ የምርጫ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ኮሚቴው ዕለታዊ የመረጃ ልውውጥ በማካሄድ የሚናበብ ነው ብለዋል።

ዕቅድ ተዘጋጅቶ በፌደራልና በክልል አስተዳደሮች ዘንድ የተሰራጨ ሲሆን ፣  እስከ ዞን ድረስ ለጸጥታ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተከውኖ ወደ ሥራ መገባቱ ነው የተገለጸው።

እጩዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ታዛቢዎች፣ የምርጫ አስፈጻሚ አካላት፣ የምርጫ ቁሳቁስ፣ የምርጫ ጣቢያዎች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግላቸውና ሂደቱ ያለ እንቅፋት እንዲከናወን የጸጥታ አካላት  በየስፍራው ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የምርጫ ቁሳቁስ  የማሰራጨት ሥራ የጸጥታ እክል ከሚስተዋልባቸው አንዳንድ ስፍራዎች በስተቀር በመላው ሀገሪቱ መከናወኑ ተመላክቷል።

ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንዳመላከተው በምርጫ ሂደቱ በመንግሥት ላይ  የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ተመልክቶ ፈጣን የመፍትሄ ምላሽ መስጠትም የኮሚቴው አንዱ ሥራ መሆኑ ነው፡፡