የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ ምርጫ እንዲራዘም ያቀረቡት ጥሪ ብልህነት የጎደለው እጅግ አደገኛ ነው – ሎረንስ ፍሪማን

ሎረንስ ፍሪማን

ሚያዝያ 30/2013 (ዋልታ) – “የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ ምርጫ እንዲራዘም ያቀረቡት ጥሪ ብልህነት የጎደለው እጅግ አደገኛ ነው” ሲሉ ባለፉት 30 ዓመታት በአፍሪካ ፖለቲካ-ኢኮኖሚክ ጉዳይ ተንታኝነት የሚታወቁት ሎረንስ ፍሪማን ገለጹ።

ሎረንስ ፍሪማን ‘አፍሪካ ኤንድ ዘ ወርልድ’ በተሰኘው ድረ-ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ በኢትዮጵያ የሚካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፍሬይ ፌልትማን በቀጣናው ጉብኝት ለማድረግ በሚገኙበት ዋዜማ አምስት ሴናተሮች የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተ በጻፉላቸው ደብዳቤ ምርጫው እንዲራዘም ጠይቀዋል።

እንደ ፍሪማን ገለጻ፤ ሴናተሮቹ በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ በቂ ግንዛቤ የላቸውም፡፡ በመሆኑም ምርጫው እንዲራዘም መጠየቃቸው አደገኛ መሆኑን እንዳልተረዱ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምዕራባውያንን ጫና ወደጎን በመተው ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር መሆኗን በማስረገጥ ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን እውን እንዲጠቀሙ ማድረግ እንዳለባት ያስገነዘበው ጽሁፉ፤ ሴናተሮቹ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ የተለየ ባህሪ እንዳልተገነዘቡ ጠቅሷል።

ሴናተሮቹ የኢትዮጵያን የ125 ዓመት የታሪክ ጉዞ እንኳን መለስ ብለው እንዳልተገነዘቡ የጠቆመው ጽሁፉ፤ የአድዋ ድል ከተመዘገበበት ከ1888 ዓ.ም የዳግማዊ ምኒሊክ ዘመን ጀምሮ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሚመራው ጎሳን መሰረት ያላደረገው ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል ያደረጉትን ጥረት ማየት ቢችሉ መልካም እንደነበር ገልጿል።

ይህንን ማየት ያልቻሉት ሴናተሮቹ ደብዳቤያቸውን የጻፉት በዜና ዘገባዎችና በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ላይ ተመስርተው እንደሆነ መረዳት እንደሚቻል አብራርቷል።

ሴናተሮቹ በጻፉት ደብዳቤ ያሰፈሩት ሃሳብ መሬት ላይ የሌሉና ተጨባጭ ያልሆኑ ጉዳዮችን እንደሆነ ያነሳው ጽሁፉ፤ “በአሁኑ ወቅት በርካታ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ምርጫው የሚታመንበትና ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ከምርጫው ለመታቀብ መወሰናቸውን አስታውቀዋል” በሚል በደብዳቤው የተጠቀሰውን ጉዳይ በአብነት አንስቷል።

ሴናተሮቹ ይህንን ጉዳይ ማንሳታቸውና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በመጋፋት ምርጫው እንዲራዘም መጠየቃቸው የሚያስቆጣ ተግባር መሆኑን ፍሪማን በጽሁፋቸው ገልጸዋል።

“እኔ እስከማውቀው ድረስ ከምርጫው ራሱን ያቀበው አንድ ፓርቲ ብቻ ነው” ያሉት ፍሪማን፤ የሴናተሮቹ ደብዳቤ ሌሎችም ከምርጫው እንዲወጡ ብልጥነት የጎደለው ሽፋን የመስጠት ድርጊት እንደሚመስል ጠቁመዋል።

ምርጫው እንዲራዘም ለቀረበው የሴናተሮቹ ጥሪ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ አመርቂ ምላሽ ለልዩ መልዕክተኛው ፌልትማን መስጠታቸውን አውስተዋል።

አምባሳደር ፍጹም በምላሻቸው ምርጫው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሽግግር እውን የሚሆንበት ታሪካዊ አጋጣሚ እንደሚሆንና ከዚህ በፊት ከነበሩት ምርጫዎች ሁሉ የተሻለ እንዲሆን መንግስት ብዙ ርቀት መጓዙን መግለጻቸውን አስታውሰዋል።

ሎረንስ ፍሪማን በጽሑፋቸው የሴናተሮቹ ደብዳቤ በምርጫው ሂደት የሚሳተፉ ፓርቲዎች ድምጽ ቢያጡም ‘አልተሸነፍንም’ እንዲሉ እድል ሊሰጥ የሚችል አደገኛ ደብዳቤ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ደብዳቤው ብልህነት የጎደለውና ችግር ሊያመጣ የሚችል መሆኑን አስገንዝበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።