የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ግቡን ኢንዲደርስ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ የላቀ መሆን አለበት ተባለ

ሐምሌ 11/2014 (ዋልታ) በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የገጠር ልማት አስተባባሪ አብዱራህማን አብደላ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ግቡን ኢንዲደርስ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ የላቀ መሆን አለበት አሉ።

አስተባባሪው ይህን ያሉት በኦሮሚያ ክልል የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር እንደ አርሲ ዞን በሄጦሳ ወረዳ እየተካሄደ ባለበት ነው።

ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብ ግቡን ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በዞኑ በዛሬው ዕለት 32 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ የችግኝ ተከላው እየተካሄደ መሆኑን የአርሲ ዞን ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ገና መሐመድ ተናግረዋል።

በአርሲ ዞን ባለፈው ዓመት የተተከለው ችግኝ 87 በመቶ መጽደቁንም ተናግረዋል።

የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ ሙሳ ፉሮ በበኩላቸው በዞኑ በዘንድሮ ዓመት 224 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የያዝነውን ዕቅዳችንን ለማሳካት በዛሬው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርኃ ግብር እውን ማድረግ አለብን ብለዋል።

በችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉት የአርሲ ዞን ነዋሪዎች በነብስ ወከፍ የተሰጠንን የችግኝ መጠን በመትከል የመሪያችንን አደራ እናሳካለን ብለዋል።

በዱጋሳ ፉፋ (ከአርሲ)