የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽል የልማት ፖሊሲ ይፋ ሆነ

ሚያዝያ 30/2013 (ዋልታ) – የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚረዳ የአርብቶ አደር ልማት ፖሊሲና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ በሰላም ሚኒስቴር አማካኝነት ተዘጋጅቶ ይፋ ሆኗል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ስዮም መስፍን የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከ12 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖርበት አካባቢና ከ60 በመቶ በላይ የሀገሪቱን የቆዳ ስፋት የሚሸፍን ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ የማህበረሰቡን ህይወት ለማሻሻል የሚረዳ ፖሊሲ እንዳልተዘጋጀ ገልጸዋል።

ስትራቴጂው በአርብቶ አደሩ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ፣ የአርብቶ አደሩን የኑሮ ተግዳሮቶች ያገናዘበ እና በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎችን የዳሰሰ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ፖሊሲው የእንሰሳቱን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ሌሎች የገቢ ምንጮችን መፍጠር እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ በልማት መንደር ማሰባሰብ ስራዎችን በማከናወን የአርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶችንና ከተሞችን በማስፋፋት የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማዘመን ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም ተጠቁሟል።

የአርብቶ አደር ልማት ፖሊሲና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂው ከሚመለከታቸው አስፈፃሚ አካላት ጋር ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ የአርብቶ አደሩን አቅም እና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንደሚያግዝም ተገልጿል፡፡

የአርብቶ አደር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት የካቲት 21/2012 ዓ.ም ባካሄደው 80ኛ መደበኛ ስብሰባ የፀደቀ ነው ተብሏል፡፡

(በቁምነገር አህመድ)