በኢትዮጵያ በዓመት 11 ሺህ እናቶች በወሊድ ምክንያት እንደሚሞቱ ተገለጸ

29ኛው አለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀን

ሚያዝያ 30/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ በዓመት 11 ሺህ እናቶች በወሊድ ምክንያት እንደሚሞቱ ተገለጸ፡፡

29ኛው አለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀን በኢትዮጵያ የሚድ ዋይፎች ማህበር አዘጋጅነት በአበበች ጎበና የእናቶች እና ህፃናት ሆስፒታል ተከብሯል።

“መረጃው ግልፅ ነው ትኩረት ለሚድዋይፎች” በሚል እየተከበረ ባለው ዝግጅት በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉጌታ እንዳለ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት 11ሺህ በቀን 30 እናቶችን እንዲሁም በዓመት ከ5ሺህ በላይ ጨቅላ ህፃናት በወሊድ ምክንያት እንደሚሞቱ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ እየታየ ያለውን በወሊድ ምክንያት የሚሞቶ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ለሚድዋይፍ ባለሙያዎች ትኩረት እና ክብር ሊሠጣቸው እንደሚገባም ተናግረዋል። ለዚህም መንግስት ከቁጥር ባለፈ ጥራት ያላቸውን ባለሙያዎችን ለማፍራት በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሚዲ ዋይፎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዘነበ አካለ በዓሉን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር መንግስት አንድም እናት እንዳትሞት በሚል እየሰራ ባለው ስራ የሚድዋይፎች ቁጥር እንደ ሀገር 17ሺህ የደረሠ ቢሆንም፤ ይህ ቁጥር ግን በቂ ባለመሆኑ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል። በዚህም ለሚድዋይፎች ትኩረት መሥጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ሚዲ ዋይፎች ማህበር አዲስ አበባ ቻምበር ፕሬዝዳንት ሲስተር አስቴር ህይወት የሚሠጡ እናቶችን ህይወት ለመታደግ ሚድዋይፎችን በሚገባ ልንጠቅም እና የሚያስፈልጋቸውን ልናሟላ ይገባል ብለዋል።

በበዓሉ ላይ በሙያው ረዥም ዓመታትን የሠሩ አንጋፋ እና ወጣት ሚዲዋይፎች የተገኙ ሲሆን፣ የእውቅና እና የሽልማት ፕሮግራም ተካሂዷል።

ከተመሠረተ 30 ዓመታትን ሊያከብር ጥቂት ጊዜያት የቀረው የኢትዮጵያ ሚድ ዋይፎች ማህበር 7ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን፣ በመላው ሀገሪቱ ቅርንጫፎችን ከፍቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

(በድልአብ ለማ)