የአሸባሪው ህዋሃት የውጭ ጉዳይ ተወካዮች ሳምሪ የተባለውን የገዳይ ቡድንና በሱዳን ለልዩ ተልዕኮ እያዘጋጇቸው ያሉ ታጣቂዎችን ለቀጣይ ስምሪት እያዘጋጁ መሆኑ ተገለጸ

ነሀሴ 10/2013 (ዋልታ) – የቀድሞ የአሸባሪው ህዋሃት አመራር የነበሩትና አሁን ላይ የሽብር ቡድኑ የውጭ ጉዳይ ተወካዮች የሆኑት አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ እና ፍስሃ አስገዶም የተባሉት በቅርቡ ወደ ሱዳን ካርቱም በመምጣት የገዳይ እስኳድ ቡድን የሆነውን የሳምሪ ወጣቶች ቡድን አባላትንና በሱዳን ለልዩ ተልዕኮ ቡድኑ እያዘጋጃቸው ያሉ ታጣቂዎችን በአካል በማግኘት የሞራል ግንባታና የቀጣይ ስምሪት አቅጣጫዎች ላይ ዉይይት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምንጮች ገለጹ።
እነዚህ ግለሰቦች አስፈላጊውን የገንዘብና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ከሽብርተኛው ህወሃት እንደሚያገኙ ቃል የገቡላቸው ሲሆን፤ በተጨማሪም በቆይታቸው እነዚህ የጁንታው አመራሮች በሱዳን የሚገኙ እንደ ራሻይዳ ያሉ የህገወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን በማግኘት ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ሚስጥራዊ ድርድር ማድረጋቸውን ተረጋግጧል።
ለዚህ ሴራቸው ስኬትም በስደተኞችካምፖች ላይ የተለያዩ የመቀስቀሻና የማነሳሻ የተሃድሶ ዝግጅቶችን እያተጠቀሙ መሆኑን ምንጮቻችን በቪዲዮ አስደግፍው አረጋግጠዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በሱዳን አሁን ያለውን ውስጣዊ ትርምስን እንደምቹ አጋጣሚ በመውሰድና የሱዳንን አንድ አንድ ባለስልጣናት የዓላማቸው ተጋሪ የሆኑትን ከጎናቸው በማሰለፍ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር የጥቅም ተጋሪ የሆኑና ደስተኛ ካልሆኑት እንደ ግብፅ ካሉ ሀገራት ጋር በህቡእ ግንኙነት በመፍጠር አሁንም ተመሳሳይ ወረራና ትንኮሳ ለመፈፀም በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ የኢፕድ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ የጥሞና ግዜ እንዲያገኝና አርሶ አደሩም የክረምቱን ዝናብ በአግባቡ ተጠቅሞ ማሳውን እንዲያለማ መንግስት በሆደ ሰፊነት የወሰደውን የተናጥል የተኩስ አቁም እርምጃ ሽብርተኛው ህወሃት ይህን እድል እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድና እድሉ እንዳያመልጠኝ በማለት በአፋር ክልል ያደረገውን አይነት ተመሳሳይ ትንኮሳና ወረራ ከአማራ ክልል ህዝብ ጋርም የማወራርደው ሂሳብ አለኝ በሚል ስሌት
ፈፅሞታል፡፡
የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል እንዲህ አይነት መጠነ ሰፊ የሆነ ወረራ ሲፈፅም በሱዳን በኩል የመውጫ ኮሪደር በማመቻቸት ለሽብር እንቅስቃሴው ይረዳው ዘንድ ሱዳንን የወታደራዊና የፖለቲካዊ ማዕከል ማድረግ፤ እንደለመደው ሀብት መዝረፍ የማሸሽ፤ሰብዓዊ ክብርን በማርከስና በማዋረድ ሴቶችንና ህፃናትን የመድፈር አሁን ላይ እያደረገ ያለውን የጅምላ ግድያ በማካሄድ የብቀላ በትሩን ማሳረፍ ነው ዓላማው፡፡
ቡድኑ ታዲያ ይህንን እኩይ የጥፋት ሴራውን እውን ለማድረግ በራያ ቆቦና በወልዲያ በኩል እያደረገ ካለው ትንኮሳና ወረራ በተጨማሪ በሁመራና በማይፀብሪ ባሉ ግንባሮችም በተከታታይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ቢሰነዝርም፤በድንበሩና በመሬቱ ድርድር የማያውቀው ጀግናው የአማራ ህዝብ፣ልዩ ሀይሉና ታጣቂው እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወረራና ትንኮሳውን በጣምራ በመመከትና የአፀፋ እርምጃ በመውሰድ የሽብር ቡድኑን ፍላጎት አምከነውታል ነው ያሉት፡፡
ይህ አልሳካለት ያለው አሸባሪው ህወሃት የጥፋት ተልዕኮውን እውን ለማድረግ ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን በማማተር በጦርነቱ ወቅት በስደተኛ ስም ሀሻባና ግንዳማ በተባሉና በሌሎችም በሱዳን በሚገኙ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ አስርጎ ያስገባቸውን እንደ የሳምሪ ወጣቶች ያሉ ገዳይ እስኳድና ልዩ ሀይልም ጭምር የሚገኙበትን ሰብስቦ በማደራጀት፣ በማስልጠንና በማስታጠቅ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በሁመራ በኩል ዘልቀው እንዲገቡና ወረራና ጥቃት እንዲፈፅሙ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም፤ በድንበር ላይ በሚገኘው በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እየተደመሰሱና የሃፍረት ካባቸውን እየተከናነቡ ተመልሰዋል ብለዋል፡፡