የአንበጣ መንጋ በመኸር ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ

አቶ በላይነህ ንጉሴ

ሚያዝያ 14/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ በመኸር ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሴ እንደገለጹት ቀደም ካለው ተሞክሮ በመነሳት አሁንም ተከስቶ ጉዳት እንዳያስከትል በተደራጀ መልኩ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።

የአንበጣ መንጋው በመኸር ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በአሁኑ ወቅት የተጠናከረ የመከላከል ስራ በመሰራቱ እና ወቅቱ ለመፈልፈል ምቹ ባለመሆኑ ስርጭቱ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ከአጎራባች አገራት ይገባ የነበረው የአንበጣ መንጋ መቀነሱንም ጠቁመዋል።

በእድገት ደረጃው እንቁላል መጣል የጀመረ ቢኖርም እንዳይራባ ለማድረግ የተጠናከረ የቁጥጥርና አሰሳ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በመከላከሉ ሂደት የባለሙያዎችን አቅም ከማሳደግ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ሲሰራ እንደነበር ጠቁመው፣ ካለፈው አመት ዝግጅት አንጻር ሲታይም አሁን ላይ የተሻለ መሆኑን አብራርተዋል።

በኬሚካል ርጭት ወቅት ሲያጋጥም የነበረው የባለሙያዎች አልባሳት እጥረትም ተቀርፎ በበቂ ሁኔታ እንዲሟላ መደረጉን ያነሱት አቶ በላይነህ፣ በሚጠረጠሩ ቦታዎች በአውሮፕላን ቅኝት እየተደረገ መሆኑንና በተለይም ኪስ ቦታዎች ላይ ደግሞ ሄሊኮፕተር በመጠቀም አሰሳ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ አምስት ክልሎችና በድሬዳዋና አካባቢው ቀደም ሲል ተከስቶ በነበረው የአንበጣ መንጋ 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል የሰብል ምርት ላይ ጉዳት አድርሶ አልፏል።

ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች  የዘር ወቅት ከመድረሱ በፊት ግብዓት መሰራጨቱን ጠቅሰው፣ በቀጣይ የዘር ሽፋኑን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአፍሪካ መጠነ ሰፊ ሰብል ያወደመው የአንበጣ መንጋ ዳግም አንሰራርቶ ጉዳት እንዳያስከትል በትብብርና በቅንጅት የመከላከል ስራው መጠናከር እንዳለበት ይታመናል።

ከ25 ዓመታት ወዲህ የከፋ ነው የተባለለት የበረሃ አንበጣ ላለፉት በርካታ ወራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ያሉ አገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል።

ከሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አንበጣን የመቆጣጠር ስራ ሲሰራ ቢቆይም ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ መነሻውን ከየመንና ሱማሌላንድ አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ጉዳት አድርሷል።

መንጋው ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ እና ሶማሊያን ክፉኛ ጎድቶም አልፏል።