ኢትዮ ቴሌኮም በ8100 A ከደንበኞቹ የሰበሰበውን ከ122 ሚሊየን ብር በላይ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስረከበ

ሚያዝያ 14/2013 (ዋልታ) – ኢትዮ ቴሌኮም በ8100 A ከደንበኞቹ የሰበሰበውን 122 ሚሊየን 467 ሺህ 676 ብር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስረከበ።

ኢትዮ ቴሌኮም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ጋር በመሆን በ8100 A አጭር የፅሁፍ መልዕክት መላኪያ ቁጥር አማካይነት ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ከደንበኞቹ ሲያሰባስብ የቆየ ሲሆን፣ 122 ሚሊየን 467 ሺህ 676 ብር ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ደንበኞች የሰበሰበው መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ 3ኛው ዙር የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ካለፉት ሁለት ዙሮች ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ገልፀው፣ በአጠቃላይ በ3ቱ ዙሮች 252 ሚሊየን ብር ከደንበኞች ለህዳሴ ግድብ ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚዋ የተሰበሰበውንም ገንዘብ ለኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻ አስረክበዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፣ እስካሁን በቦንድ ግዢ እና በልገሳ 15 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በሀገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ከሚገኙ ዜጎች መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በ8100ም ሆነ በሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክቶች ሁሉም ዜጋ እንዲሳተፍ ተጠይቋል።

(በትዕግስት ዘላለም)