የአውሮፓ ህብረት ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት 149 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ

ሚያዚያ 15 /2013 (ዋልታ) – የአውሮፓ ህብረት በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በፈረንጆቹ 2021 ላጋጠመው የሰብአዊ ቀውስ ድጋፍ የሚውል 149 ሚሊየን ዩሮ መመደቡን አስታወቀ።

የህብረቱ የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽነር ጃኔች ሉናርቺች እንደተናገሩት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቀጠናው ካጋጠሙ የአየር ጸባይ ለውጥ፣ የአንበጣ መንጋ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋት ባሻገር መጠነ ሰፊ ግጭቶችና መፈናቀሎች ያሉበት ነው።

በዚህም አስቸኳይ የህይወት አድን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የምግብ የመጠለያና የጤና አገልግሎት እገዛ ሊደረግላቸው ይገባል ማለታቸውን ሪሊፍ ዌብ የተባለ ድረገጽን ጠቅሶ ኢዜአ አስነብቧል።

በኮሚሽኑ የድጋፍ ድልድል መሰረት ሶማሊያ 45 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ ሱዳን 52 ሚሊዮን፣ ኡጋንዳ 32 ሚሊዮን እና ጅቡቲ ግማሽ ሚሊዮን ዩሮ የተመደበላቸው ሲሆን ቀሪውን ስምንት ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ በጋራ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝን መከላከል ይውላል ተብሏል።

ኮሚሽነር ሌናርቺች በሰሞኑ ወደ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ለኢትዮጵያ 53 ነጥብ 7 ሚሊየን እና ለደቡብ ሱዳን 43 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ለሰብአዊ ድጋፍ እገዛ እንዲሆናቸው መስጠቱ ይታወሳል።