ፌዴሬሽኑ ከውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ጋር የአጋርነት የውል ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

ሚያዚያ 15 /2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ጋር ሕክምናን በተመለከተ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በሰጡት አስተያየት ስምምነቱ በፌዴሬሽኑ የሚዘጋጁ ወደ ሰባት የሚጠጉ ውድድሮችን እንዲሁም ከ100 በላይ ለሚሆኑ የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እድሉን ይፈጥራል ብሏል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የውዳሴ ዲያግኖስቲግ ማዕከል በብሔራዊ ቡድኖች ትጥቆችና በተለያዩ የስታዲየሞች ዝግጅትና የተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖች ላይ ማዕከሉን የሚያስተዋውቅበት እድል ተመቻችቷል፡፡

የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ባለቤት እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳዊት ኃይሉ ከፌዴሬሽኑ ጋር ባደረጉት ስምምነት ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡
(ምንጭ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን)