የአውሮፓ ሕብረት አገራት በዩናይትድ ኪንግደም ላይ የጣሉትን የጉዞ እገዳ እንዲያነሱ አሳሰበ

የአውሮፓ ሕብረት 27 አባል አገራት ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር በተያያዘ የተጣሉ ገደቦችን በተመለከተ የተባበረ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሞክሩ አስታወቁ።

ይህን ያሉት በዩናይትድ ኪንግደም ከተገኘው አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ጋር ተያይዞ በርካታ አገራት የጉዞ እገዳ መጣላቸውን ተከትሎ ነው።

የአውሮፓ ኮሚሽን፤ አገራት የጣሉትን የጉዞ እገዳ እንዲያነሱና ወሳኝ የሆኑ ጉዞዎችን እንዲጀምሩ ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።

ይሁን እንጂ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት በድንበር ቁጥጥር ላይ የራሳቸውን ሕግ ለማስቀመጥ ነጻ በመሆናቸው በራሳቸው ፖሊሲዎችም ይህንን ማድረግ ሊቀጥሉ ይችላሉ።

አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ከነባሩ በበለጠ ይበልጥ ተስፋፊ ሲሆን፤ የበለጠ ገዳይ ስለመሆኑ ግን የሚያመላክት ማስረጃ የለም።

የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ሁሉም በሚባል ደረጃ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚደረግ የጉዞ እገዳ እየጣሉ ነው።

የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን፤ አባል አገራቱ የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርጉ ወይም ራሳቸውን እንዲያገሉ በማድረግ ሰዎች ወደ የሚኖሩበት አገራቸው እንዲሄዱ መፍቀድ አለባቸው ብሏል። ነገር ግን አስፈላጊ ያልሆነ ጉዞ ሊበረታታ እንደማይገባ ገልጿል።

የተሰጡት ምክረ ሃሳቦችም ለሕብረቱ አምባሳደሮች የሚቀርብ ሲሆን አባል አገራቱ የሚጥሏቸውን ገደቦች ከግምት ያስገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ምንም እንኳን ይህ ምክረ ሃሳብ ቢሰጥም፤ አገራት በራሳቸው ፖሊሲዎች እቀባውን የመቀጠል እድላቸው ሰፊ መሆኑን የቢሲው ጋቪን ሊ ከብራስልስ ዘግቧል።

በሌላ በኩል የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋዎች ኃላፊ ማይክ ርያን “አዲሱ የቫይረስ ዝርያ የወረርሽኙ ዝግመተ ለውጥ መደበኛ አካል ነው። ከቁጥጥር ውጭም አልሆነም” ብለዋል።

ይህ ንግግራቸው ግን ከዚህ ቀደም የዩኬው የጤና ሚኒስትር ማት ሃንኮክ ከተናገሩት ጋር የሚቃረን ነው ተብሏል።

በዩኬ እየተሰጠ ያለውን የፋይዘር ክትባት አምራች የሆነው የባዮንቴክ ተባባሪ መስራች ኡጉር ሳሂን በበኩላቸው ብሩህ ተስፋን ሰንቀዋል።

ኡጉር “በሳይንሳዊ መልኩ ከክትባቱ የሚገኘው የበሽታ መከላከያ ምላሽ አዲሱን የቫይረስ ዝርያ ሊቋቋም ይችላል” ብለዋል።

አዲሱን ዝርያ የሚከላከል ክትባት በስድስት ሳምንታት ውስጥ ሊሰጥ ይችላል ማለታቸውን ቢቢሲ አስነብቧል ፡፡