እስራኤል በሁለት ዓመት ውስጥ ለ4ኛ ጊዜ ምርጫ ልታደርግ ነው

እስራኤል በስልጣን ላይ ያለው የጥምር መንግሥት በአገራዊ በጀት ጉዳይ ሊስማማ ባለመቻሉ ወደ ምርጫ ለመግባት መገደዷ ተገለጸ።

ምርጫው የሚካሄደው መንግስቱን የመሰረቱት ሁለቱ ፓርቲዎች በበጀት ጉዳይ ላይ ባለመስማማታቸው ነው ተብሏል፡፡

መራጮች ከ12 ወራት በኋላ በመጋቢት ወር ዳግም ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንደሚያቀኑ ነው የተገለጸው፡፡

ይህን ተከትሎም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሊኩይድ ፓርቲ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ቤኒ ጋንትዝ ፓርቲ እርስ በእርስ እየተወነጃጀሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

እስራኤል ባለፉት ጊዜያት ያካሄደቻቸው ምርጫዎች አሸናፊውን ፓርቲ በማያሻማ ሁኔታ ነጥለው የሚለዩ አልሆኑም።

የሙስና ክስ ያለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለ6ኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመናቸውን መቀጠል የሚፈልጉ ሲሆን፣ ኔታንያሁ “የተመሰረተብኝ ክስ ሐሰተኛና ፖለቲካዊ አሻጥር ያለው ነው” ሲሉ አስተባብሏል።

ማክሰኞ የእስራኤል ፓርላማ መበተኑ ተገልጿል፡፡ ይህም የሆነው የ2021 አገራዊ በጀት ላይ ፓርቲዎች መስማማት ባለመቻላቸው የአገሪቱ ሕግ በሚያስገድደው መሰረት ፓርላማው ለመበተን ተገዷል።

ፓርላማው እንዳይበተን ለማድረግ ባለቀ ሰዓት ውይይቶች ቢደረጉም አልተሳኩም ነው የተባለው።

ከዚህ ቀደም የተካሄዱት ሁለት ምርጫዎች አሸናፊ ባለመኖሩ መንግስቱን የመሩት በጥምረት እንደነበር ይታወሳል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትርነቱንም ቦታ በፈረንጆቹ ህዳር ወር 2021 ቤኒ ጋንትዝ እንደሚይዙት ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡