የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር ገለጸ

አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ

መጋቢት 26/2015 (ዋልታ) የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር በልማት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሠራ ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በዘርፈ ብዙ የትብብር አድማሶች ላይ ጠንካራ አጋርነት እንዳለው ገልጸው የኅብረቱ አባል አገራትም ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸውና ግንኙነቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ግንኙነቱ በአንድ ዘርፍ ብቻ ላይ የተንጠለጠለ አለመሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ አጋርነቱ በፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ መስክም እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በተለይም ሰው ተኮር በሆኑ በማኅበራዊ ዘርፎች ላይ አውሮፓ ኅብረትና አባል አገራት ትኩረት ሰጥተው ትብብሩን ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ ለማኅበራዊ ልማት የሚውል ከ9 ነጥብ 5 እስከ 10 ቢሊዮን ብር በላይ የድጋፍ ሥምምነት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ግብርናውን ለማዘመንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታከናውናቸውን ተግባራት ለመደገፍ በኅብረቱ የሚደረገው እገዛ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።