38ኛው የኢጋድ ልዩ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) 38ኛ ልዩ ጉባኤ በወቅቱ ሊቀመንበር የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ሰብሳቢነት ታኅሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በጅቡቲ ተካሂዷል።
በጉባኤው ላይ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌህ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ሙዩጋይ ኬንያታ፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ፣ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ርብቃ ኒያንዴንግ ማቢዮር እንዲሁም በኢትዮጵያ የዑጋንዳ አምባሳደር ርብቃ አሙጌ ኦቴንጎ ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐመት፣ የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወካዮች እና የአምባሳደሮች ኮሚቴ፣ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ ነገዎ (ዶ/ር)፣ የኢጋድ የደቡብ ሱዳን ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር እስማኤል ዋኢስ፣ የኢጋድ የቀይ ባሕር፣ የኤደን ባሕረ ሰላጤ እና ሶማሊያ አምባሳደር መሐመድ ዓሊ ጉዮ ተገኝተው ነበር።
ጉባኤው ሱዳንን በተመለከተ በአገሪቱ ለውጥ ከመጣ ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቋል።
የሱዳን ሕዝብ እና መንግሥት ከሚመለከታቸው ወገኖች የጁባ የሰላም ስምምነት መፈረማቸውን አድንቆ፣ ስምምነቱ በእምነት እና በተሟላ በተሟላ መልኩ እንዲፈጸም ብሎም ባለድርሻ አካላት የሽግግር ወቅት ሕግ አውጭ ምክር ቤት በአፋጣኝ እንዲመሠርቱ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም የሱዳን መንግሥት አሜሪካ ከያዘቻቸው አሸባሪነት የሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ በመውጣቱ በይነ መንግሥታቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።
ደቡብ ሱዳን ጋር በተያያዘ አገሪቱ በአዲስ መልክ የተዋቀረ ብሔራዊ የሽግግር አንድነት መንግሥት፣ የአስተዳደር መዋቅር በማቋቋሙ እና አሁንም በተቀመጠው ማእቀፍ የሰላም ውይይት እንደገና በመጀመሩ እንዲሁም በመንግሥት መዋቅር ምሥረታው ላይ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርቧል።
ጉባኤው በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ቴኒ (ዶ/ር) ላይ የጉዞ እቀባ አለማድረጉን አመልክቷል።
ጉባኤው በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ስለተካሄደው ዘመቻ አስመልክቶ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀረበ ማብራሪያ ያዳመጠ ሲሆን፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ የአገሪቱ መረጋጋት እና አንድነት ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን አስምሮበታል።
የኢፌዴሪ መንግሥት ሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት ከተመድ ጋር “ገደብ የለሽ፣ ቀጣይነት ያለው እና አስተማማኝ መግቢያ” እንዲኖር የሚያስችል ስምምነት መድረሱን ተቀብሏል።
ሶማሊያን በተመለከተ አገሪቱ በመጪው የካቲት ወር ውስጥ ፌዴራላዊ ምርጫ ለማካሄድ እያካሄደችው ያለውን ዝግጅት እና በሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት እና በፌዴራሉ አባላት አመራሮች መካከል መስከረም 2013 ዓ.ም ውስጥ የተፈረመውን ስምምነት እና ፕሮቶኮል መቀበሉን ገልጾ፣ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የአገሪቱ የፀጥታ ኃይል በሶማሊያ ከተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ጋር በመቀናጀት አልሸባብን ለመግታት እና ለመዋጋት ያደረገውን ጥረት አድንቋል።
የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት እና ሶማሌላንድ የጋራ ውይይት እንደገና መጀመራቸውን አድንቆ፣ የቀጠናው አገራት ውይይቶችን በማስተናገዳቸው እና በማስተባበራቸው ምስጋጋና አቅርቧል።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ኅብረት ኢጋድ ወረርሽኙን መግታት እንዲችል ለሰጠው አፋጣኝ ምላሽ ምስጋና አቅርቧል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኮቪድ-19 ክትባት ሚዛናዊ፣ ፍትሐዊ እና ጊዜውን በጠበቀ መልኩ እንዲዳረስ ለማድረግ በአንድ ላይ እንዲቆም ብሎም የአፍሪካ አገራት የድርሻቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንዲይዝ ጠይቋል።
በመጨረሻም በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና በተከሰቱ አደጋዎች ለተጎዱ ዜጎች ጊዜውን የጠበቀ ሰብአዊ እርዳታ ምላሽ እንዲሰጥ አቅጣጫ አስቀምጧል፤ የኢጋድ የሚኒስትሮች ኮሚቴ የአደጋ ምላሽ ፈንድ እንዲቋቋም ከዓመታት በፊት ያሳለፈውን ውሳኔ ማጽደቁንም ከኢጋድ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።