125ኛው የአድዋ የድል በዓል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት እየተከበረ ነው

የካቲት 22/2013 (ዋልታ) – “አድዋ የህብረ ብሄራዊ አንድነት መገለጫ ነው” በሚል መሪ ቃል የአድዋ ድል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት እየተከበረ ይገኛል፡፡

በአከባበሩ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ከበደ ዴሲሳ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሃደ ስንቄዎች፣ ጀግኖች አርበኞች፣ አርቲስቶችና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሂሩት ካሳው በመክፍቻ ንግግራቸው የአድዋ ድል ለመላው ጥቀር ህዝቦች ኩራትና የነፃነት አርማ መሆኑን ገልጸው፣ ለፀባችን መንስኤ የሆኑ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግረን መፍታት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ከአድዋ አንድነትና ትብብርን ልንማር ይገባል ሲሉም አክለዋል።

የአድዋን የስኬት ታሪካችንን ማወቅ፣ መውረስና ለትውልድ ማሻገር ይኖርብናል ያሉት ዶ/ር ሂሩት፣ ስኬቱን እንደ አባይ ግድብ ባሉ ትብብር በሚጠይቁ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ መድገም ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳነት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያዊነት ስጦታ ሳይሆን ዋጋ ተከፍሎበት፣ ተለፍቶበት ኢንዲሁም አጥንትና ደም የተከፈለበት በመስዋትነት የተገነባ ማንነት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አዲሱ ትውልድ በኢኮኖሚ የበለፀገች እና ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ በነፃነት የሚኖርባት ኢትዮጵያን በመገንባት የራሱን አድዋ ሊደግም እንደሚገባም አቶ ሽመልስ አሳስበዋል፡፡
(በትዕግስት ዘላለም)